የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ዘጠነኛ ሳምንት ዛሬ ይጀመራል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ዘጠነኛ ሳምንት ዛሬ ይጀመራል
አዲስ አበባ፤ ሕዳር 19/2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ዘጠነኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ውሎ ሁለት ጨዋታዎች ይካሄዳሉ።
ከረፋዱ 4 ሰዓት ላይ ሃዋሳ ከተማ ከሲዳማ ቡና በአበበ ቢቂላ መታሰቢያ ስታዲየም ይጫወታሉ።
ሃዋሳ ከተማ በሊጉ ካደረጋቸው ስምንት ጨዋታዎች መካከል ስድስቱን ሲያሸንፍ ሁለት ጊዜ ተሸንፏል። 16 ግቦችን በጨዋታዎቹ ላይ ሲያስቆጥር ሰባት ጎሎችን አስተናግዷል። ቡድኑ በ18 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ይዟል።
ተጋጣሚው ሲዳማ ቡና በበኩሉ በውድድር ዓመቱ ሰባት ጨዋታዎችን አድርጎ ሁለት ጊዜ ድል ሲቀናው በተመሳሳይ ሁለት ጊዜ ተሸንፏል። ሶስት ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥቷል። ሰባት ግቦችን ከመረብ ጋር ሲያገናኝ አምስት ግቦች ተቆጥረውበታል።
አንድ ተስተካካይ ጨዋታ የሚቀረው ሲዳማ ቡና በዘጠኝ ነጥብ ዘጠነኛ ደረጃን ይዟል።
በሌላኛው መርሃ ግብር ድሬዳዋ ከተማ ከይርጋጨፌ ቡና ከቀኑ 7 ሰዓት በአበበ ቢቂላ መታሰቢያ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ድሬዳዋ ከተማ በሊጉ ባካሄዳቸው ስምንት ጨዋታዎች ሶስት ጊዜ ሲያሸንፍ አምስት ጊዜ ተሸንፏል። ስምንት ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ 13 ጎሎች ተቆጥረውበታል። ቡድኑ በዘጠኝ ነጥብ 10ኛ ደረጃን ይዟል።
አዲስ አዳጊው ይርጋጨፌ ቡና በበኩሉ ከሰባት የሊጉ ጨዋታዎች መካከል ሁለቱን ሲያሸንፍ በተመሳሳይ ሁለት ጊዜ ሽንፈትን አስተናግዷል። በአራት ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይቷል። በጨዋታዎቹ ላይ ሶስት ግቦች ሲያስቆጥር ስድስት ግቦችን አስተናግዷል።
ይርጋጨፌ ቡና በ10 ነጥብ ሰባተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ የዘጠነኛ ሳምንት መርሃ ግብር እስከ ሕዳር 21 ቀን 2018 ዓ.ም ይቆያል።
ኢትዮ ኤሌክትሪክ በ24 ነጥብ ሊጉን እየመራ ነው። ባህር ዳር ከተማ እና አዲስ አበባ ከተማ 13ኛ እና 14ኛ ደረጃን ይዘው ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛሉ።
የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነቱን የኢትዮ ኤሌክትሪኳ ዳግማዊት ሰለሞን በ16 ግቦች ትመራለች። የኢትዮጵያ ንግድ ባንኳ መሳይ ተመስገን በአምስት ግቦች ትከተላለች።