የባንዳነት ተልእኮ ተቀብሎ ለጥፋት የሚንቀሳቀሰውን ፅንፈኛ ቡድን በመታገል በኩል ሕዝቡ ከጸጥታ ሃይሉ ጋር እየሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የባንዳነት ተልእኮ ተቀብሎ ለጥፋት የሚንቀሳቀሰውን ፅንፈኛ ቡድን በመታገል በኩል ሕዝቡ ከጸጥታ ሃይሉ ጋር እየሰራ ነው
ወልዲያ፤ ህዳር 19/2018(ኢዜአ)፦ የባንዳነት ተልእኮ ተቀብሎ ለጥፋት የሚንቀሳቀሰውን ፅንፈኛ ቡድን በመታገል በኩል ህዝቡ ከጸጥታ ሃይሉ ጋር በመሆን በጋራ እየሰራ መሆኑን በአማራ ክልል የሰሜን ወሎ ዞን አስተዳደር ገለጸ።
የሕዝብ ጠላትና የልማት ጸር በሆነው ጽንፈኛ ቡድን ላይ ሕግ የማስከበር ስራው ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑንም አስተዳደሩ አስታውቋል።
በአማራ ክልል በዞን፣ በወረዳ እና ከተሞች የተለያዩ የማሕበረሰብ ክፍሎች ተወካዮች በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ሰሞኑን ተከታታይ ውይይቶችን አድርገዋል።
በሰሜን ወሎ ዞንም የመንግስት ሰራተኞች፣ የኃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎችና ሌሎችም ተመሳሳይ ውይይት ማድረጋቸው ይታወቃል።
አጠቃላይ የነበረውን ውይይትና በተሳታፊዎች የተነሱ ሃሳቦች ምን ይመስላሉ፣ ምንስ ውጤት ተገኘባቸው በማለት ኢዜአ የሰሜን ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አራጌ ይመርን አነጋግሯል።
ዋና አስተዳዳሪውም በየመድረኮቹ ከሕዝቡ የተነሱ ነጥቦችና ጥቅል አስተያየቶች የፅንፈኛ ቡድኑን የጥፋት እንቅስቃሴ የሚያጋልጡ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በአማራ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች በመንቀሳቀስ ዘረፋ፣ ግዲያ እና እገታ የሚፈፅመው ጽንፈኛ ቡድን የሕዝብ ጠላትና የልማት ጸር መሆኑን በተለያዩ ማሳያዎች ከየመድረኮቹ መነሳቱን አስታውሰዋል።
በመሆኑም የባንዳነት ተልእኮ ተቀብሎ ለጥፋት የሚንቀሳቀሰውን ጽንፈኛ ቡድን ሕብረተሰቡ ከጸጥታ ኃይሉ ጋር በመተባበር እንደሚታገሉት ያረጋገጡበት መድረክ ነበር ብለዋል።
የፅንፈኛ ቡድኑ ዓላማ ሕጻናት እንዳይማሩ፣ እናቶች በጤና ተቋም እንደይወልዱና አጠቃላይ በሕብረተሰቡ ዘንድ ሰላምና መረጋጋት እንዳይፈጠር መሆኑን በየመድረኮቹ በማንሳት በፅናት እንደሚታገሉት መናገራቸውን ገልጸዋል።
ከጥፋት በመውጣት የመንግስትን የሰላም አማራጭ በመቀበል እድሉን መጠቀም እንደሚገባም በተደጋጋሚ ተነስቷል ብለዋል።
አጠቃላይ ሕዝባዊ የውይይት መድረኮቹ የሰላምን አስፈላጊነት አጽንኦት በመስጠት የተጀመሩ የልማት ስራዎች ተጠናክረው የሚቀጥሉበት ሁኔታ ላይ የጋራ አቋም የተያዘበት መሆኑን ገልጸዋል።
በዚሕም የባንዳነት ተልእኮ ተቀብሎ ዘረፋ፣ እገታና ግድያ በሚፈፅመው ፅንፈኛ ቡድን ላይ የተጠናከረ እርምጃ የሚወሰድ መሆኑን አረጋግጠው፤ የሰላም አማራጭ የሚከተሉትንም ለመቀበል ዝግጁ ነን ብለዋል።