የአፈር ለምነትን በዘላቂነት ማሻሻል የሚያስችል የተፈጥሮ ማዳበሪያ በስፋት እየተዘጋጀ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአፈር ለምነትን በዘላቂነት ማሻሻል የሚያስችል የተፈጥሮ ማዳበሪያ በስፋት እየተዘጋጀ ነው
ባሕር ዳር፤ ሕዳር 19/2018 (ኢዜአ)፦ በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን የሰብል ምርታማነትን ይበልጥ ለማሳደግ የአፈር ለምነትን በዘላቂነት ማሻሻል የሚያስችል የተፈጥሮ ማዳበሪያ በስፋት እየተዘጋጀ መሆኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ ገለጸ።
በመምሪያው የሰብል ልማትና ጥበቃ ቡድን መሪ አንዱዓለም አያሌው፤ አርሶ አደሩ የተፈጥሮ ማዳበሪያ በማዘጋጀት ምርታማነቱን እንዲያሳድግና የዘመናዊ ማዳበሪያ ወጭን እንዲቀንስ ለማገዝ እየተሰራ መሆኑን ለኢዜአ ተናግረዋል።
በዚህም ዘንድሮ አምስት ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ የተፈጥሮ ማዳበሪያ በማዘጋጀት ከ140 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ላይ ለመጠቀም ታቅዶ ወደ ተግባር መገባቱን ገልጸዋል።
ከ160 ሺህ በላይ አርሶ አደሮችን በማሳተፍ በሚካሄደው የተፈጥሮ ማዳበሪያ ዝግጅትም እስካሁን አራት ነጥብ ዘጠኝ ሚሊየን ሜትር ኪዩብ ማዘጋጀት መቻሉን ጠቅሰዋል።
በተጨማሪም የባዮ ጋዝ ተረፈ ምርት ከሆነው ሳለሪ ከ14 ሺህ ሜትር ኪዩብ በላይ የተፈጥሮ ማዳበሪያ እንደተዘጋጀ ጠቁመው፤ የ"ቨርሚ ኮምፖስት" የማዘጋጀት ስራ እየተከናወነ መሆኑን አስረድተዋል።
ከእንስሳት ተረፈ ምርት፣ ከቅጠላ ቅጠልና ሌሎች የአካባቢ ቁሳቁሶች የሚዘጋጀው የተፈጥሮ ማዳበሪያ አርሶ አደሩ ለዘመናዊ ማዳበሪያ የሚያውለውን ወጭ በመቀነስ ምርታማነት በማሳደግ ተጠቃሚ በመሆን ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በዞኑ ጓንጎ ወረዳ የብዝራካኒ ቀበሌ አርሶ አደር መኮንን ፈንታሁን በሰጡት አስተያየት፤ ያዘጋጀቱን 30 ኩንታል የሚሆን የተፈጥሮ ማዳበሪያ በመጪው የምርት ወቅት አንድ ሄክታር መሬታቸውን በግብአትነት ለመጠቀም ማቀዳቸውን ተናግረዋል።
ባለፉት ዓመታት የተፈጥሮ ማዳበሪያ አዘጋጅተው በመጠቀማቸው ለዘመናዊ ማዳበሪያ የሚያወጡትን ወጭ ከመቀነሳቸው ባሻገር የመሬታቸውን ለምነት በማሻሻል ምርታማ እንዲሆን ማስቻሉንም አውስተዋል።
በዚሁ ወረዳ የአንጓይ ቀበሌ አርሶ አደር አልጋነህ አካል፤ ዘንድሮ አንድ ሄክታር ተኩል ለመሸፈን የሚያስችል የተፈጥሮ ማዳበሪያ ለማዘጋጀት አቅደው እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።
ይህም የዘመናዊ ማዳበሪያ ወጪን በመቀነስ ምርታማነትን ለማሳደግ እንደሚያስችላቸው ገልጸዋል።
ከግብርና መምሪያው የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው፤ በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን በባለፈው በጀት ዓመት አምስት ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ የተፈጥሮ ማዳበሪያ በማዘጋጀት ከ138 ሺህ ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ በግብአትነት ጥቅም ላይ ውሏል።