በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከ65 ሺህ ሔክታር በላይ መሬት በበጋ መስኖ ይለማል - ኢዜአ አማርኛ
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከ65 ሺህ ሔክታር በላይ መሬት በበጋ መስኖ ይለማል
አዲስ አበባ፤ ሕዳር 19/2018 (ኢዜአ)፡- በዘንድሮው የበጋ መስኖ ልማት ሥራ 65 ሺህ 347 ሔክታር በተለያዩ ሰብሎች እንደሚለማ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ ባበከር ኸሊፋ ተናገሩ።
ኃላፊው ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ በክልሉ የተለያዩ ወረዳዎች የበጋ መስኖ ሥራ መጀመሩን አስታውቀዋል።
ከበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ጋር በተያያዘ በክልሉ ለስንዴ ልማት ተስማሚ ተፈጥሯዊ ሁኔታ ባላቸው ወረዳዎች 1 ሺህ 202 ሔክታር ይለማል ብለዋል።
እስካሁን እየተከናወነ ባለው ሥራም 445 ሔክታር በበጋ ስንዴ ዘር መሸፈኑን አረጋግጠዋል።
ከዚህ ውስጥ በክላስተር እየለማ ያለው 222 ሔክታር መሆኑንም ጠቁመዋል።
በዘንድሮው የበጋ መስኖ ልማት ሥራ ለማልማት ከታቀደው 65 ሺህ 347 ሔክታር ውስጥ 10 ሺህ 557 ሔክታሩ በክላስተር እንደሚለማም ነው ያመላከቱት።
እስካሁን ባለው የበጋ መስኖ ልማት ሥራ 9 ሺህ 487 ሔክታር በተለያዩ ሰብሎች ዘር መሸፈኑን አስረድተዋል።
በአጠቃላይ የመስኖ ተጠቃሚዎች ቁጥር 13 ሺህ 386 መሆኑንም ነው የገለጹት።