ጤናማ የአመጋገብ ስርዓት ! - ኢዜአ አማርኛ
ጤናማ የአመጋገብ ስርዓት !
በጾምና ጾም በማይኖርበት ወቅት ያለ የአመጋገብ ሥርዓት በሰውነት ጤና ላይ የየራሱ ተጽዕኖ ስላለው በአግባቡ መደረግ እንዳለበት ይመከራል።
ጾም በሳይንስ የተደገፉ ጥቅሞች እንዳሉት እና የጤና አንድ አጋር እየሆነ መምጣቱንም በዲላ ዩኒቨርሲቲ የምግብ ሳይንስና ኒውትሬሽን መምህር፣ ተመራማሪ እና ደራሲ ይሁኔ አየለ ለኢዜአ ተናግረዋል።
በተጨማሪም ከበርካታ በሽታዎች እራስን በመጠበቅ ጤናማ ሕይወት ለመምራት እንደሚረዳ ታውቆ በስፋት የኑሮ ዘይቤ አካል እየሆነ ስለመምጣቱም አመላክተዋል።
በጾም ወቅት ሰውነት እራሱን ያጸዳል፤ ይህም በብዙ መልኩ ጤናማ ሕይወት እንዲኖር ያስችላል ይላሉ።
ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመከላከል ወይም በይበልጥ እንዳይወሳሰቡ ለማድረግ ጾም ከፍተኛ ጥቅም እንዳለው በዘርፉ የተደረጉ ምርምሮች ማመላከታቸውንም አንስተዋል።
በተለይም ክብደትን እና በሰውነት ውስጥ ያለ የስብ ክምችትን ለመቀነስ ብሎም ከፍተኛ ደም ግፊትን፣ እንዲሁም የስኳር መጠንን ለመቆጣጠር ጾም አንድ የሕይዎት ዘዬ እየሆነ ነው ብለዋል።
በሌላ በኩል በጾም ወቅት ሰውነት ስለሚደክም እና የሚፈልገው ፈሳሽ እጥረት ስለሚያጋጥም በቀላሉ የሚፈጩ እና ሰውነት የሚፈልገውን ፈሳሽ ማስገኘት የሚችሉ ምግቦችን መጠቀም እንደሚገባ መክረዋል።
በዚሁ መሠረት ከጾም በኋላ ምግብ በሚበላበት ሠዓት እንደ ጁስ፣ ሾርባ፣ አጥሚት፣ ሰሊጥ፣ ሱፍ፣ ተልባ፣ ኑግ፣ አትክልትና ፍራፍሬዎችን መጠቀም ተገቢ ነው ይላሉ።
በተጨማሪም በፕሮቲን ይዘታቸው የበለጸጉ የጥራጥሬ ዓይነቶችን (ባቄላ፣ አተር፣ ምሥር) በደንብ በማብሰል መጠቀም እንደሚመከርም አንስተዋል።
ጾም ከመፍታት በፊት (ከምግብ በፊት ውኃ መጠጣት) ድርቀት የነበረበትን የሰውነት ክፍል እርጥበት እንዲኖረውና ለተሳለጠ የምግብ መፈጨት ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል ነው ያሉት።
በተቻለ መጠን ስብጥራቸው በርከት ያሉ የምግብ ዓይነቶችን መመገብ አንዱ የሌለው ንጥረ ነገር ከሌላኛው ስለሚገኝ በዚህ አግባብ መመገብ እንደሚመከርም አስረድተዋል።