አመራሩ ትብብርና አብሮነቱን በማጠናከር ለልማት መትጋት አለበት - ኢዜአ አማርኛ
አመራሩ ትብብርና አብሮነቱን በማጠናከር ለልማት መትጋት አለበት
ሀዋሳ፤ ሕዳር 18/2018 (ኢዜአ) ፡- በየደረጃው ያለው አመራር በተግባርና አስተሳሰብ ትብብርና አብሮነቱን በማጠናከር ለልማትና ለሕዝብ አገልግሎት መትጋት አለበት ሲሉ የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ደስታ ሌዳሞ አስገነዘቡ።
"በመደመር መንግስት ዕይታ የዘርፎች እመርታ" በሚል መሪ ሀሳብ ላለፉት ዘጠኝ ቀናት በሀዋሳ ከተማ ለክልሉ ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች ሲሰጥ የቆየው ስልጠና ተጠናቋል።
ስልጠናው መጠናቀቁን ተከትሎ ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ እንደገለጹት፤ አመራሩ በስልጠናው ያገኘውን ዕውቀት በአግባቡ ወደ ተግባር በመለወጥ በክልሉ የተጀመረውን ሁለንተናዊ የብልጽግና ጉዞ ዕውን ለማድረግ ጠንክሮ መስራት ይጠበቅበታል።
በየደረጃው ያለው አመራር በተግባርና አስተሳሰብ ትብብርና አብሮነቱን በማጠናከር ለልማትና ለሕዝብ አገልግሎት መትጋት አለበት ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በየአካባቢው ያሉ እምቅ ሃብቶችን በማልማት ምርታማነትን በማሳደግ ከተረጅነት መውጣት የጋራ ግብ አድርገን በትብብር መስራት አለብን ብለዋል።
በክልሉ በሁሉም መስኮች ተስፋ የተሰነቀባቸው የልማት እንቅስቃሴዎች እንዳሉ አንስተው፤ እነዚህን ከዳር ማድረስና ለስኬት ማብቃት ይገባል ሲሉም አክለዋል።
በከተሞች የተጀመረውን የኮሪደር ልማት ስራና ሌሎች መሰረተ ልማቶችን በአግባቡ በማስፋፋት ከተሞችን የብልጽግና ማዕከል የማድረግ ስራ አፅንኦት የተሰጠው ተግባር መሆኑንም አንስተዋል።
የሴቶችንና የወጣቶችን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚነታቸውን የሚያረጋግጥና አሳታፊ የግብርናና ገጠር ልማት ስራዎችን በማጠናከር ወደላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ርብርብ ማድረግም እንዲሁ።
በክልሉ በተለይም የአገልግሎት፣ የኢንዱስትሪ፣ የቱሪዝም፣ የዲጅታላይዜሽንና ሌሎችም የልማት ተግባራት ተጠናክረው የሚቀጥሉ መሆኑንም ርዕሰ መስተዳድሩ አረጋግጠዋል።
በንግዱ ዘርፍ የሚስተዋለውን ሕገወጥነት በመከላከል የዋጋ ንረትን የማርገብና ገበያን የማረጋጋት ተግባርም ልዩ ትኩረት ይደረግበታል ብለዋል።
ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር ተያይዞ የሚነሱ ቅሬታዎችን መፍታት የሚያስችለው መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል።
በዚህ ሁሉ ሂደትም አመራሩ በላቀ ብቃትና ቁርጠኝነት መስራትና እቅዶቹን ለውጤት ማብቃት ይጠበቅበታል በማለት አስገንዝበዋል።