ከፍተኛ የወባ ስርጭት ባለባቸው አንዳንድ አካባቢዎች የበሽታ መከላከልና መቆጣጠር ስራው ተጠናክሮ ቀጥሏል - ኢዜአ አማርኛ
ከፍተኛ የወባ ስርጭት ባለባቸው አንዳንድ አካባቢዎች የበሽታ መከላከልና መቆጣጠር ስራው ተጠናክሮ ቀጥሏል
አዲስ አበባ፤ ሕዳር 18/2018(ኢዜአ)፦ ከፍተኛ የወባ ስርጭት ምጣኔ ባለባቸው አካባቢዎች ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ ያለው የወባ መከላከልና መቆጣጠር ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን የጤና ሚኒስቴር ገለፀ።
የጤና ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እንዲሁም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን የሚያካሂደው አራተኛው ዙር የወባ ጠቋሚ ጥናት ማስጀመሪያ መርኃ ግብር በቢሾፍቱ ተካሂዷል።
የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ እንዳሉት የበሽታ መከላከልን መሰረት ባደረገ ስራ የኤች አይ ቪ፣ ወባና ቲቢ በሽታ የስርጭት ምጣኔ ላይ መቀነስ ታይቷል።
ሆኖም ባለፉት ጥቂት ዓመታት በተለያዩ ምክንያቶች በአንዳንድ አካባቢዎች የወባ ምጣኔ ከፍ ማለቱን ተከትሎ ርብርብ ሲደረግ መቆየቱን አንስተዋል።
የህብረተሰቡን ግንዛቤ የማሳደግ፣ የአልጋ አጎበር ስርጭትና የፀረ-ወባ ኬሚካል ርጭት ስራዎች በስፋት መከናወናቸውን ገልፀዋል።
በዚህም የወባ ስርጭት ምጣኔ አምና ከነበረበት ጋር ሲነጻጸር በ40 በመቶ መቀነስ ችሏል ነው ያሉት።
የወባ ከፍተኛ ምጣኔ ባለባቸው አካባቢዎች ትኩረት ተደርጎ የበሽታውን ስርጭት ለመከላከልና ለመቆጣጠር እየተከናወነ ያለው ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ የወባ ጠቋሚ ጥናት በሁሉም ክልሎች እንደሚካሄድ ተናግረዋል።
ጥናቱ እስካሁን የወባ በሽታን ለመከላከል እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን ውጤታማነት የሚገመግምና ለቀጣይ ዓመታት የሚሰራባቸውን ስትራቴጂዎችና የመንግስት እቅድ የሚያመላክት የመረጃ ምንጭ እንደሚሆን ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሳይ ሀይሉ በበኩላቸው ኢንስቲትዩቱ የህብረተሰብ ጤና አደጋዎችን የመከላከልና መቆጣጠር እንዲሁም የምርምር ስራ እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።
አራተኛው ዙር የወባ ጠቋሚ ጥናት ወባን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ሲከናወኑ የነበሩ ተግባራት ጥንካሬና ድክመትን ለመለየትና ቀጣይ አቅጣጫን ለማሳየት የሚረዳ መሆኑንም ገልፀዋል።
የኢንስቲትዩቱ ተመራማሪ ዶክተር አዱኛ ወዬሳ በበኩላቸው ጥናቱ ቤት ለቤት የሚካሄድና በ268 መረጃ ሰብሳቢ ባለሙያዎች የሚካሄድ መሆኑን ጠቁመዋል።
ከ14ሺህ በላይ አባወራዎችና እማወራዎች የሚሳተፉበት ጥናቱ ዓለም አቀፋዊ መስፈርቶችን የተከተለ መሆኑንም አስረድተዋል።