ለህብረ ብሔራዊ አንድነት መጠናከርና ለሀገር ግንባታ የሚተጋ ትውልድ የማፍራት ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል - ኢዜአ አማርኛ
ለህብረ ብሔራዊ አንድነት መጠናከርና ለሀገር ግንባታ የሚተጋ ትውልድ የማፍራት ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል
አዲስ አበባ፤ ህዳር 18/2018(ኢዜአ)፦ ለኢትዮጵያ ህብረ ብሔራዊ አንድነት መጠናከርና ለሀገር ግንባታ የሚተጋ ትውልድ የማፍራት ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዘላለም ሙላቱ(ዶ/ር) ገለጹ።
የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ 20ኛውን የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀንን በማስመልከት ከበዓሉ ጋር ተያያዥነት ባላቸው ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የፓናል ውይይትና የተማሪዎች ጥያቄና መልስ ውድድር አካሂዷል።
በተማሪዎች መካከል በተካሄደው የጥያቄና መልስ ውድድር አሸናፊ የሆኑ ተማሪዎች የአጋዥ መጽሐፍት፣ የታብሌትና የምስክር ወረቀት ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዘላለም ሙላቱ(ዶ/ር)፥ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን የኢትዮጵያውያንን አብሮ የመኖር እሴት የሚያጎለበት መሆኑን ተናግረዋል።
ይህ የአብሮ መኖር ህብረ ብሔራዊ እሴት ከትውልድ ወደ ትውልድ በአግባቡ እንዲተላለፍ የትምህርት ተቋማት ትልቅ ሀገራዊ ኃላፊነት አለባቸው ብለዋል።
ሀገርን የሚገነባ ትውልድ ማፍራት ላይ አበክሮ መስራት ከሁሉም ይጠበቃል ነው ያሉት።
ለዚህም ከመደበኛው ትምህርት ባለፈ በልዩ ልዩ መንገዶች ተማሪዎች ስለ ኢፌዲሪ ህገ መንግስት የተሻለ ግንዛቤ የሚያገኙበትን መድረክ ማጠናከር እንደሚገባ ገልጸዋል።
ህብረ ብሔራዊ አንድነትንና አብሮነትን የሚያጠናክሩ እንደ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን አይነት ሁነቶች ላይ ትውልዱን ማሳተፍ የኢትዮጵያን ብዝኃነትና የአብሮነት እሴቶች የተገነዘበ ሀገር ወዳድ ዜጋ ማፍራት ያስችላል ብለዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባኤ ፋይዛ መሃመድ በበኩላቸው፥ 20ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ኢትዮጵያውያን የሀገር ፍቅር ስሜትና ህብረ ብሔራዊ አንድነታችንን የምናጸባርቅበት ነው ሲሉ ገልጸዋል።
ትውልዱ ስለ ሀገሪቱ ህገ መንግስታዊ ስርዓት የተሻለ ግንዛቤ እንዲኖረው ምቹ አጋጣሚ በመሆኑ በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባ አንስተዋል።
የትምህርት ማህበረሰቡ ቀኑን በተለያዩ ሁነቶች ማክበሩ ስለብሔር ብሔረሰቦች ባህል፣ ስለብዝኃነትና ህብረ ብሔራዊ አንድነት ጠንካራ ግንዛቤ ያለው ትውልድ መገንባት የሚያስችል በመሆኑ የሚበረታታ ነው ብለዋል።
በመድረኩ የተሳተፉት የክሩዝ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የዓለም ባንክ ቅርንጫፍ ርዕሰ መምህር ሱራፌል ዐቢይ፥ ተማሪዎች ከህገ መንግስት ጋር በተያያዙ ጉዳዮች እንዲሁም ሀገራችን ያላትን ባህልና ወግ እንዲገነዘቡ ከመደበኛው ትምህርት ባለፈ በክበባት አማካኝነት የማስረፅ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።
የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀንን ምክንያት በማድረግ ተማሪዎች የጥያቄና መልስ ውድድር ማድረጋቸው የተሻለ ግንዛቤ የሚፈጥሩ በመሆናቸው ሊጠናከሩ እንደሚገባ የገለጹት ደግሞ የአየር አምባ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ከበደ አሰፋ ናቸው።
በተማሪዎች የጥያቄና መልስ ውድድር አንደኛ የወጣችው የክሩዝ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ሳራ አህመዲን በውድድሩ አንደኛ በመውጣቷ መደሰቷ ገልጻ፥ ስለ ሀገሯ ህብረ ብሔራዊነት፣ ስለ ዴሞክራሲ ስርዓትና ስለ ህገመንግስቱ እውቀት መቅሰሟን ተናግራለች።
በውድድሩ ሁለተኛ የወጣችው የእቴጌ መነን የልጃገረዶች አዳሪ ትምህርት ቤት የ8ኛ ክፍል ተማሪዋ ሰሚራ ንጋቱ በበኩሏ፥ በውድድሩ ህገመንግስቱንና የብሔር ብሔረሰቦች ቀን በተመለከተ የተሻለ ግንዛቤ ማግኘቷን ገልጻለች።