በኦዶ ሻኪሶ ወረዳ ህብረተሰቡን ያሳተፈ የትምህርት ተደራሽነትና ጥራት ማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ - ኢዜአ አማርኛ
በኦዶ ሻኪሶ ወረዳ ህብረተሰቡን ያሳተፈ የትምህርት ተደራሽነትና ጥራት ማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ
አዶላ፤ ህዳር 17/2018(ኢዜአ)፦ በጉጂ ዞን ኦዶ ሻኪሶ ወረዳ በህብረተሰብ ተሳትፎ የታገዘ የትምህርት ተደራሽነትና ጥራት ማሳደጊያ ተግባራት በመከናወን ላይ መሆናቸውን የወረዳው ትምህርት ጽህፈት ቤት ገለጸ፡፡
የጽህፈት ቤቱ ሀላፊ አቶ ግርማ ሮቤ እንዳሉት በትምህርት ለሁሉም ኢንሸቴቭ የትምህርት ተደራሽነትንና ጥራትን ለማረጋገጥ የባለድርሻ አካላትና የህብረተሰብ ተሳትፎን ማጠናከር ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው።
ለአብነትም ባለፈው አመት ግንባታቸው የተጀመሩ 14 ትምህርት ቤቶች ተጠናቀው ስራ መጀመራቸውን አንስተዋል።
ግንባታቸው ተጠናቆ የመማር ማስተማር ስራን ከጀመሩ መካከል ሶስቱ መደበኛ ሲሆኑ ቀሪዎቹ ደግሞ የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች መሆናቸውን ተናግረዋል።
ትምህርት ቤቶቹ የመምህራን፣ የአስተዳደር ጽህፈት ቤቶችና የስፖርት ማዘውተሪያንም ያካተቱ መሆናቸውን አክለዋል፡፡
የትምህርት ቤቶቹ መገንባት 3 ሺህ 500 አዳዲስ ተጨማሪ ተማሪዎችን ለመቀበል ከማገዛቸው ባለፈ በክፍል ጥበት የሚፈጠረውን የመማር ማስተማር እንከን እንደሚፈቱም አክለዋል።
ለትምህርት ቤቶቹ ግንባታ ህብረተሰቡ 75 ሚሊዮን ብር የሚገመት የአይነት፣ የጉልበትና የገንዘብ ድጋፍ አድርጓል ብለዋል፡፡
በወረዳው የትምህርት ጥራትና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ከአዳዲስ ግንባታዎቹ በተጨማሪ የ89 መማሪያ ክፍሎች እድሳት፣ 81 የመምህራን መኖሪያ ቤት ግንባታ እንዲሁም የምድረ ግቢ ውበትና የአጥር ስራ መከናወኑን ጠቅሰዋል፡፡
ለትምህርት ጥራት የትምህርት ቤቶችን ደረጃ የማሻሻል ፣ የውሃ፣ የመብራትና የመንገድ መሰረተ ልማት የማሟላት ስራም እየተካሄደ ነው ብለዋል፡፡
ለዚህም በህብረተሰቡ ተሳትፎ የ25 የገጠር ትምህርት ቤቶች ደረጃ መሻሻሉንና መሰረተ ልማት መሟላቱን አስታውሰዋል።
የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ እንደ ክልል የተነደፈውን የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶችን የማስፋት ስራንም እውን የማድረግ ስራም ተጠናክሮ መቀጠሉን ጠቁመዋል፡፡
በሻኪሶ ወረዳ የበቴ ትምህርት ቤት መምህር ብርሃኑ ተሾመ እንዳሉት ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ ህብረተሰቡ የድርሻውን እየተወጣ ነው፡፡
በተለይም በህዝብ ተሳትፎ እየተሰሩ ያሉ ትምህርት ቤቶችና የመምህራን መኖሪያዎች የመምህሩን የስራ ተነሳሽነት ማሳደጋቸውን ጠቅሰዋል፡፡
የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ማሻሻል በእውቀት የበቁ ተማሪዎችን ለማፍራት የማይተካ ሚና በመኖሩ ወላጆች ከመንግስት ጋር በመተባበር እያካሄዱት ያለው ተግባር ምስጋና የሚቸረው መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
መምህር ገመዳ ጉድሩ በበኩላቸው የመማሪያ ክፍል መሰራታቸው የተማሪዎችን መጨናነቅ በማቃለል ለበርካታ ህጻናት የመማር እድል እንዲያገኙ የሚረዳ ነው ብለዋል፡፡
በዚህም የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎቸ ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ገልጸዋል፡፡