ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን ይበልጥ ማጠናከር የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን ይበልጥ ማጠናከር የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው
አዲስ አበባ፤ ሕዳር 18/2018(ኢዜአ)፦ የጋራ ትርክትን በመገንባት ሕብረ ብሔራዊ አንድነት እና የፌዴራሊዝም ሥርዓትን ይበልጥ ማጠናከር የሚያስችሉ ተግባራት በመከናወን ላይ እንደሚገኙ ተገለጸ።
"ዴሞክራሲያዊ መግባባት ለሀገራዊ አንድነት" በሚል መሪ ሀሳብ 47ኛው የጉሚ በለል መድረክ ዛሬ በአዲስ አበባ ከተማ ተካሂዷል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የጨፌ ኦሮሚያ አፈ ጉባዔ ሰአዳ አብዱራህማን ባደረጉት ንግግር፤ የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ለብዙ ዓመታት ያደረጉት ትግል ለሁሉም የምትሆን፣ ሁሉንም የምትመስል እና ሁሉንም በእኩልነት የምታስተናግድ ሀገር ለመገንባት ነው ብለዋል።
ይህንን በተግባር ለማረጋገጥ በተለይ የለውጡ መንግስት የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ባሕል፣ ወግ እና ታሪክ እንዲከበር በማድረግ የጋራ ትርክትን እያጠናከረ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በሁሉም አቅጣጫ የገዘፈ ታሪክ፣ ውብ ማንነት፣ ብዝኃ መልክ፣ ባሕል፣ ቋንቋና እሴት ያላት፤ በልዩነት ውስጥ ባለው ውበትና አንድነት የምትደምቅ ሀገር መሆኗን ገልጸዋል።
በልዩነት ውስጥ ያለውን ሕብረ ብሔራዊ አንድነት በጋራ ትርክት በማጠናከር ሀገርና ሀገራዊ እሴትን ለመገንባት መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በክልሉ አሰባሳቢ የሆኑ የጋራ ትርክትን በመገንባት ሕብረብሔራዊ አንድነትና የፌዴራሊዝም ሥርዓትን ይበልጥ ማጠናከር የሚያስችሉ ተግባራት በመከናወን ላይ እንደሚገኙም ገልጸዋል።
የኦሮሚያ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ኃይሉ አዱኛ በባኩላቸው እንደተናገሩት፤ በነጠላ ትርክት የተፈጠሩ ችግሮችን በመፍታት ወደ ዴሞክራሲ የሚደረገው ሽግግር ተስፋ ሰጪ ነው።
ተግዳሮቶችን በሀገራዊ ምክክር ለመፍታት እየተሰራ ያለው ተግባር የጋራ ትርክትን ይበልጥ ለማጠናከር የላቀ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል መከበር እህትማማችነትና ወንድማማችነትን ከማጠናከር ጎን ለጎን ነጠላ ትርክት በማሸነፍ እንደ ክልልም ሆነ እንደ ሀገር የጋራ ትርክት ለመገንባት ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ገልጸዋል።
ጠንካራ ሕብረ ብሔራዊ አንድነትና ፌዴራሊዝምን በአስተማማኝ መሰረት ላይ የመገንባት ታላቅ ግብን ለማሳካት እየተደረገ ያለውን ጥረት በመደገፍ ሁሉም የበኩሉን መወጣት እንደሚጠበቅበትም አንስተዋል።
በመድረኩ ላይ ምሁራን ጥናታዊ ጽሁፎችን አቅርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።