ቀጥታ፡

3ኛው የኢጋድ የሚዲያ ሽልማት በአዲስ አበባ መካሄዱ የኢትዮጵያን የልማት ስኬቶችና ቀጣናዊ ሚናዋን አጉልቶ ለማሳየት መልካም አጋጣሚ ይፈጥራል

አዲስ አበባ፤ ህዳር 18/2018(ኢዜአ)፦ 3ኛው የኢጋድ የሚዲያ ሽልማት በአዲስ አበባ መካሄዱ የኢትዮጵያን የልማት ስኬቶችና ቀጣናውን ለማስተሳሰር እያከናወነቻቸው ያሉ ውጤታማ ተግባራትን አጉልቶ ለማሳየት መልካም አጋጣሚ እንደሚፈጥር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

ኢጋድ ኢትዮጵያ የዘንድሮውን የሚዲያ አዋርድ እንድታስተናግድ መምረጡ በአረንጓዴ ዐሻራ እና ሌሎች የአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ስራዎች ላከናወነቻቸው ስኬታማ ተግባራት እውቅና የሰጠ መሆኑንም ገልጿል።

የኢጋድ የሚዲያ ሽልማት የፊታችን ቅዳሜ እና እሁድ በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብያት ጌታቸው በሰጡት መግለጫ የሚዲያ ሽልማቱ ከአረንጓዴ ልማትና ከአየር ንብረት ጥበቃ ጋር በተያየዙ ጉዳዮች ላይ ትኩረት የሚያደርግ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ኢትዮጵያ የሽልማት መርኃ ግበሩን ለማዘጋጀት መመረጧ በአረንጓዴ ዐሻራ፣ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ የአየር ንብረት ለውጥ ምላሽ አመራር ውስጥ እያበረከተች ላለው ቁልፍ ሚና እውቅና የሰጠ ነው ብለዋል።

በተጨማሪም ሁለተኛውን የአፍሪካ አየር ንብረት ጉባኤ ስኬታማ በሆነ መንገድ ማስተናገዷእንዲሁም የኮፕ-32 ጉባኤን እንድታዘጋጅ ለመመረጧ እውቅና የሰጠ ምርጫ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ሽልማቱ የቀጣናውን የሚዲያ ባለሙያዎች ለማቀራረብና ቀጣናዊ ትስስሮችን ለማጠናከር የሚካሄድ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

የኢጋድ አባል ሀገራት የሚዲያ ባለሙያዎች ወደ ኢትዮጵያ በሚመጡበት ጊዜም የልማት ስኬቶችን የማስተዋወቅ፣ ኢትዮጵያ ለቀጣናው ትስስር እያከናወነቻቸው ያሉ ስራዎችን አጉልቶ ለማሳየት መልካም አጋጣሚ እንደሚፈጥርም ጠቁመዋል፡፡

ኢትዮጵያ በዘንድሮው የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ባለስልጣን(ኢጋድ) የሚዲያ ሽልማት የትኩረት መስከ በሆነው የአረንጓዴ ልማት ሥራ በአርዓያነት የሚወሰዱ ሥራዎችን አከናውናለች።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ሃሳብ አመንጪነት የተጀመረው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ቀጣናዊና አህጉራዊ የልማት አጀንዳ ሆኗል፡፡

የኢጋድ የሚዲያ ሽልማት ውድድሩ በቴሌቪዥን፣ በሬዲዮ፣ በህትመት፣ በዲጂታል ሚዲያ እና የሴቶች ዘርፍን ጨምሮ በስምንት መስኮች እንደሚካሄድ ታውቋል፡፡

400 የሚሆኑ የኢጋድ አባል ሀገራት የሚዲያ ባለሙያዎች ስራዎቻቸውን ለውድድር ያስገቡ ሲሆን ከዚሁ ውስጥ 94 የሚሆኑት ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች መሆናቸው ተጠቅሷል፡፡

የሽልማት ሥነ-ስርዓቱ በአዲስ አበባ መካሄዱ በፐብሊክ ዲፕሎማሲ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን በማጠናከር የኢትዮጵያን ገጽታ ለመገንባት አዎንታዊ ሚና የሚጫወት ነው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም