የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን መከበር ህብረ-ብሔራዊ አንድነትን ለማጠናከር ያግዛል - ኢዜአ አማርኛ
የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን መከበር ህብረ-ብሔራዊ አንድነትን ለማጠናከር ያግዛል
ጅግጅጋ፤ ህዳር 18/2018(ኢዜአ)፦ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ህብረ-ብሔራዊ አንድነትን በማጠናከር ረገድ ጉልህ ድርሻ መጫወቱን የሱማሌ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ አያን አብዲ ገለጹ።
20ኛው የብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን ’’ዴሞክራሲያዊ መግባባት ለህብረ ብሄራዊ አንድነት’’ በሚል መሪ ሀሳብ በሱማሌ ክልል ደረጃ ጅግጅጋ ከተማ ተከብሯል።
የክልሉ ምክር ቤት አፈጉባኤ አያን አብዲ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ለሀገር የልማትና ዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ በአንድነትና አብሮነት ላይ የተመሰረተ መግባባትን መመስረት አስገዳጅ ነው።
ህብረ ብሄራዊነት ላይ የተመሰረተ ዴሞክራሲያዊ ስርአት ለመገንባትና የጋራ እሴቶችን ጠብቆ ለማቆየት የብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን መከበር ድርሻው የጎላ ነው ብለዋል።
የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን መከበር ህብረ-ብሔራዊ አንድነትን በማጠናከር ረገድ ጉልህ ድርሻ ተጫውቷል ያሉት አፈጉባዔዋ፤ የዘንድሮውም በዓል ብዝሃነትን በሚገባ በሚያንፀባርቅ መልኩ እየተከበረ መሆኑን አንስተዋል።
የሱማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኢብራሂም ዑስማን በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ብዝሃ ባህልና እምነት ያላት አገር በመሆኗ የብሔሮች ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀንን በጋራ በማክበር ላይ እንገኛለን ብለዋል።
ከለውጡ ዓመታት ወዲህ በሱማሌ ክልል የተገኘው ሠላም የክልሉ ህዝብ በሙሉ አቅሙ በልማቱ ላይ እንዲያተኩርና ከልማቱም ተጠቃሚ እየሆነ ነው ብለዋል።
በበዓሉ የታደሙት ገራድ ኩልሚዬ ገራድ መሐመድ በበኩላቸው ፤ የብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን የህዝቦች አንድነት የሚጠናከርበት፣ ባህልና ቋንቋቸውም ይበልጥ የሚንፀባረቅበት ቀን ነው ብለዋል።
ክልሉ በሙሉ አቅሙ ወደ ልማት መግባቱን የተናገሩት ገራድ ኩልሚዬ ገራድ መሐመድ፤ በሀገር ደረጃ የተጀመሩ ትላልቅ የልማት ፕሮጀክቶችም የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያሳድጉ መሆናቸውን አንስተዋል።
በመድረኩ በብልጽግና ፓርቲ የሶማሌ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሃላፊ ኢንጂነር መሀመድ ሻሌን ጨምሮ የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎችና ሌሎች እንግዶች ተገኝተዋል። የደም ልገሳ፣ የችግኝ ተከላና ሌሎች መርሃግብሮችም የበዓሉ አካል ነበሩ።