ዘርፈ ብዙ ውጤቶች የተገኙባቸው ልማቶች ተከናውነዋል- ከንቲባ ከድር ጁሃር - ኢዜአ አማርኛ
ዘርፈ ብዙ ውጤቶች የተገኙባቸው ልማቶች ተከናውነዋል- ከንቲባ ከድር ጁሃር
ድሬዳዋ፤ ሕዳር 18/2018(ኢዜአ)፦በድሬዳዋ የህዝብን ተጠቃሚነት በተጨባጭ ያረጋገጡ እና ዘርፈ ብዙ ውጤቶች የተገኘባቸው ልማቶች ተከናውነዋል ሲሉ የአስተዳደሩ ከንቲባ ከድር ጁሃር ገለጹ።
"በመደመር መንግስት እይታ፤ የዘርፎች እመርታ" በሚል መሪ ሃሳብ የአስተዳደሩ ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች ያካሄዱትን ስልጠና ዛሬ ያጠናቀቁ ሲሆን አመራሮቹ በአስተዳደሩ የተከናወኑ ልማቶችን ተዘዋውረው ተመልክተዋል።
በተጨማሪም በደም ዕጦት አንድም ሰው መሞት እንደሌለበት መልዕክት በማስተላለፍ በአርአያነት ደም ለግሰዋል።
በስልጠናው ማጠቃላይ ላይ የተገኙት የአስተዳደሩ ከንቲባ ከድር ጁሃር፤ ባለፉት የለውጥ ዓመታት የህዝብን ተጠቃሚነት በተጨባጭ ያረጋገጡ እና ዘርፈ ብዙ ውጤቶች የተገኘባቸው ልማቶች ተከናውነዋል ብለዋል።
በግብርና ፣ በኢንዱስትሪ፣ በኮሪደር ልማት፣ በቴክኖሎጂ እና በቱሪዝም ዘርፎች እየተመዘገቡ የሚገኙ ሁለንተናዊ ውጤቶችን በላቀ ደረጃ ለማስቀጠል ርብርቡ ተጠናክሮ መቀጠሉንም ገልጸዋል።
በተለይም ከተማዋን ለስራና ለኑሮ ምቹ እያደረገ የሚገኘው የኮሪደር ልማት በስፋት እንደሚቀጥል ጠቅሰው በአራቱ የገጠር ክላስተሮች እና በደቻቱ ወንዝ ዳርቻዎችም የኮሪደር ልማቱ በቅርቡ እንደሚጀመር ተናግረዋል።
በመሆኑም አመራሩ የተገኙ ውጤቶችን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር እና የሚጀመሩ አዳዲስ ዘርፎችን በቁርጠኝነት ዳር ለማድረስ የተቀናጀ ርብርብ ማድረግ እንደሚጠበቅበት አሳስበዋል።
ለአመራሩ የተሰጠው ስልጠና ተልዕኮን በታላቅ ብቃትና ቁርጠኝነት ለመፈፀም ወሳኝ ሚና እንደሚኖረው የገለፁት ደግሞ በብልጽግና ፓርቲ የድሬዳዋ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ዩሱፍ ናቸው።
በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች በፈጠራና በፍጥነት መርህ የብልጽግና ትልሞችን ሙሉ በሙሉ በማሳካት ድሬዳዋ የንግድ፣ የኢንዱስትሪ እና የኢንቨስትመንት መዳረሻ እና የዜጎች ብልፅግና የተረጋገጠባት ለማድረግ የጀመሩትን ስራ አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
በስልጠናው እና በጉብኝቱ የተካፈሉ አመራሮች በበኩላቸው፤ የሃሳብና የተግባር አንድነትን በማፅናት እየተመዘገቡ የሚገኙ ሁለንተናዊ የልማት ውጤቶችን በላቀ ደረጃ ለማሳደግ ስልጠናው ቁጭትና መነሳሳት እንደፈጠረባቸው ለኢዜአ ገልጸዋል።
በአርአያነት ደም የለገሱት የስልጠናው ተሳታፊ አቶ አብዶ ሙሜ እና ወይዘሮ ስሜነሽ አለማየሁ እንዳሉት፤ ያላቸውን አቅም አሟጠው በመጠቀም እየተመዘጉ የሚገኙትን ውጤቶች ለማሳደግ ተዘጋጅተዋል።
በተለይም በጉብኝቱ ወቅት በአስተዳደሩ ገጠርና ከተማ ክላስተሮች የተሰሩት የልማት ስራዎች የህዝብን ተጠቃሚነት በትክክል እያረጋገጡ እንደሆኑ መመልከታቸው የበለጠ እንዲተጉ እንዳደረጋቸው ተናግረዋል።