አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የ75ኛ ዓመት በዓሉን ትናንት፣ ዛሬና ነገን በሚያሳዩ መርኃ ግብሮች ሊያከብር ነው - ኢዜአ አማርኛ
አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የ75ኛ ዓመት በዓሉን ትናንት፣ ዛሬና ነገን በሚያሳዩ መርኃ ግብሮች ሊያከብር ነው
አዲስ አበባ፤ሕዳር 18/2018(ኢዜአ)፦አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ 75ኛ ዓመት የአልማዝ ኢዮቤልዩ የምስረታ በዓሉን ያለፈበትን ታሪክ፣ አሁን ያለበትን ሁኔታ እንዲሁም የመጪ ዘመን ራዕዩን በሚያሳይ መልኩ ለማክበር ዝግጅት ማጠናቀቁን አስታውቋል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤት የኮሙኒኬሽን አማካሪ ሃና ደምሴ፣ የዩኒቨርሲቲው የቀድሞ ተማሪዎች ኔትወርክ ጽህፈት ቤት ዳይሬክተር መሳይ ገብረማርያምና የቴአትር መምህር ዘርይሁን ብርሃኑ የበዓሉን የአከባበር ዝግጅት በተመለከተ ማብራሪያ ስጥተዋል።
የኮሙኒኬሽን አማካሪዋ ሃና ደምሴ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት፤ ለ75ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ዩኒቨርሲቲው ያለፈበትን ታሪክ፣ አሁን ያለበትን ሁኔታ እንዲሁም የመጪ ዘመን ራዕዩን የሚያሳዩ ዝግጅቶች ተደርገዋል።
በዓሉ “ያለፈውን በማክበር የተሻለ ነገን ማለም” በሚል መሪ ሀሳብ በልዩ ልዩ መርኃ ግብሮች እንደሚከበርም ጠቁመዋል።
ዝግጅቶቹ በዓሉን ከመዘከር ባሻገር ተማሪዎችን፣ የዩኒቨርሲቲውን ማህበረሰብ እንዲሁም የቀድሞ የዩኒቨርሲቲውን ምሩቃንን የማገናኘት፣ የማስተዋወቅ እና የማወያየት ዕቅድን ያካተቱ ናቸው ብለዋል።
የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ እና አጋር አካላት ዩኒቨርሲቲው ከሃያ አምስት ዓመታት በኋላ የት ደርሶ ማየት እንደሚፈልጉ መልካም ምኞታቸውን በፅሁፍ በአንድ መዝገብ የሚያኖሩበት ዝግጅት መኖሩንም ጠቅሰዋል።
የዩኒቨርሲቲው የቀድሞ ተማሪዎች ኔትወርክ ጽህፈት ቤት ዳይሬክተር መሳይ ገብረማርያም በበኩላቸው፤ ከታህሳስ 18 እስከ 24/2018 ዓ.ም ባሉት ቀናት የቀድሞ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምሩቃን እና ቤተሰቦች ወደ ዩኒቨርሲቲያቸው እንዲመጡ መጋበዛቸውን አስታውቀዋል።
ከመምህሮቻቸው ጋር እንዲገናኙ፣ የተማሩባቸውን ቦታዎች እንዲጎበኙና ዩኒቨርሲቲውን ማገዝ በሚችሉባቸው ጉዳዮች ላይ ውይይት ለማድረግ መታቀዱን ገልፀዋል።
የዩኒቨርሲቲው የቴአትር መምህር ዘርይሁን ብርሃኑ፤ የዩኒቨርሲቲውን የ75 ዓመታት ጉዞና ውጣ ውረድ ሰንዶ የያዘ መፅሐፍ በዩኒቨርሲቲው እውቅ ምሁራን መጻፉንና በቅርቡ እንደሚመረቅ ተናግረዋል።
ዩኒቨርሲቲው እንደ አንድ የትምህርት እና ምርምር ተቋም ብቻ ሳይሆን በሀገሪቱ የፖለቲካ እና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ያሳረፈውን አሻራ የሚዳስስ ዘጋቢ ፊልም መዘጋጀቱን ጠቅሰዋል።
የ75ዓመት ልህቀት በ75 ሴኮንዶች የሚል የተማሪዎች የአጭር ፊልም ውድድር እንደሚካሄድም ነው የገለጹት።