የአመራሩን አቅም በማጎልበት የህዝብን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተጀመሩ ሥራዎች ይጠናከራሉ - ኢዜአ አማርኛ
የአመራሩን አቅም በማጎልበት የህዝብን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተጀመሩ ሥራዎች ይጠናከራሉ
ወላይታ ሶዶ፤ሕዳር 18/2018(ኢዜአ)፦በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የአመራሩን አቅም በማጎልበት የህዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተጀመሩ ሥራዎች እንደሚጠናከሩ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ገለጹ።
"በመደመር መንግስት ዕይታ የዘርፎች እመርታ" በሚል መሪ ሃሳብ ለክልሉ መካከለኛና ከፍተኛ አመራሮች ሲሰጥ የነበረው ስልጠና ተጠናቋል።
በስልጠናው ማጠቃለያ ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ እንደገለጹት፤ በክልሉ የአመራሩን የአስተሳሰብና የተግባር አንድነት በማቀናጀት የህዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በልዩ ትኩረት እየተሰራ ነው።
ባለፉት ጊዜያት ለአመራሩ የተሰጡ ስልጠናዎች በክልሉ ዘለቂ እድገት እንዲመዘገብ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ጠቅሰው በሁሉም መስኮች የተመዘገቡ ስኬቶች ቀጣይነት እንዲኖራቸው አመራሩን የማብቃት ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
ሁሉን አቀፍ ዕውቀት ያለው አመራር ከመፍጠር ባለፈ የአስተሳሰብና የተግባር አንድነትን በማምጣት የህዝብ ጥያቄን የመመለስ አቅም ማሳደግ እንደሚገባም አመልክተዋል።
በክልሉ ህብረብሔራዊነትን በማጠናከር ዘላቂ ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ በቅንጅት የሚሰራው ሥራ በቀጣይም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
ከስልጠናው ተሳታፊ አመራሮች መካከል አቶ ዳኘ ሂዶ፤ ስልጠናው አመራሩ ራሱን እንዲመለከትና የአካባቢውን ዕምቅ አቅም አሟጦ በመጠቀም ለህዝብ ተጠቃሚነት በትጋት እንዲሰራ ያስገነዘበና አቅም የፈጠረ ነው ብለዋል።
በቀጣይም በተቋማቸው የሀሳብና የተግባር አንድነትን በማቀናጀት ለስኬታማነት ተግተው እንደሚሰሩ ተናግረዋል።
ሌላኛው ሰልጣኝ ወይዘሮ መስከረም ወልደማርያም በበኩላቸው፤ ስልጠናው በተለያዩ ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች እንደሀገርና እንደ ክልል ያለውን አቅም ተረድተን ውጤታማ ሥራ ለመስራት እውቀት ያስጨበጠን ነው ብለዋል፡፡
በስልጠና ያገኙትን አቅም ተጠቅመው የክልሉን ጸጋ ለይቶ በማልማት የህዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ተግተው እንደሚሰሩም አረጋግጠዋል።