በክልሉ የህዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የማረጋገጥ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የህዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የማረጋገጥ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ
ጋምቤላ፤ሕዳር 18/2018(ኢዜአ)፦በጋምቤላ ክልል የልማት እቅዶችን በቅንጅት በመተግበር የህዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የማረጋገጥ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዓለሚቱ ኡሞድ አስታወቁ።
"በመደመር መንግስት እይታ የዘርፎች እመርታ" በሚል መሪ ሃሳብ ለክልሉ ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች በጋምቤላ ከተማ ሲሰጥ የቆየው የ2ኛ ዙር የአቅም ግንባታ ስልጠና ዛሬ ተጠናቋል።
ርዕሰ መስተደድሯ አለሚቱ ኡሞድ በአቅም ግንባታ ስልጠናው ማጠቃለያ ላይ እንዳሉት፡ የክልሉን እምቅ የተፈጥሮ ሃብት በማልማት የብልጽግና ጉዞን ለማሳካት የሚሰራው ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል።
የህዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያዌዎች ምላሽ ለመስጠትም በግብርና፣ በቱሪዝም፣በኢንዱስትሪና በሌሎችም ዘርፎች ያሉትን ሰፊ የመልማት አቅሞች መጠቀም ይገባል ብለዋል።
ለዚህም አመራሩ በስልጠናው ያገኘውን አቅምና ልምዱን ወደ ተግባር በመለወጥ የክልሉን ሁለንተናዊ እድገት ማሳካት እንደሚገባም አክለዋል።
አመራሩ ህዝቡን በማስተባበር በተለይም የግብርናውን ልማት በማጠናከር የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ላይ እየተከናወኑ ያሉትን ተግባራት አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።
አመራሩ ሙስናና ብልሹ አሰራሮችን በመፀየፍ ለህዝቡ ቀልጣፋ አገልግሎት በመስጠት አርአያ መሆን እንደሚገባውም አሳስበዋል።
አመራሮቹ በዘጠኝ ቀናት ቆይታቸው በግብርና ትራንስፎርሜሽን፣ በኢንዱስትሪ፣ በቱሪዝም፣ በከተሞች ልማትና ሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ የአቅም ግንባታ ስልጠና መከታተላቸው ተገልጿል።