ቀጥታ፡

በሥልጠና ያገኛችሁትን ዕውቀት ወደ ተግባር በመቀየር ለውጥ የሚያመጣ፣ እሴት የሚጨምር ሥራ መሥራት ይጠበቅባችኋል - ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ

አዲስ አበባ፤ ህዳር 18/2018(ኢዜአ)፦ መሪዎች በሥልጠና ያገኛችሁትን ዕውቀት ወደ ተግባር በመቀየር ለውጥ የሚያመጣ፣ እሴት የሚጨምር ሥራ መሥራት ይጠበቅባችኋል ሲሉ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ አስገነዘቡ።

"በመደመር መንግሥት ዕይታ፣ የዘርፎች እምርታ" በሚል መሪ መልዕክት ለአማራ ክልል ከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሮች ሥልጠና እየተሰጠ ነው።

ርዕሰ መስተዳድሩ እስካሁን በተሰጡ የሥልጠና ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የማጠቃለያ ሃሳብ የሰጡ ሲሆን በሥልጠና ያገኛችሁትን ዕውቀት ወደ ተግባር መቀየር ከቻላችሁ ለውጥ ማምጣት ይቻላል ብለዋል።


 

የግብርናውን ዘርፍ መለወጥ ግድ እንደሚል ጠቁመው ኋላ ቀር የማረሻ ዘዴንና የአስተራረስ መንገድን በቴክኖሎጂ መቀየር እንደሚገባም ተናግረዋል።

መሪዎች ለውጥ የሚያመጣ፣ እሴት የሚጨምር ሥራ መሥራት እንደሚጠበቅባቸው ጠቁመው በግብርናው ዘርፍ ለውጥ ሲመጣ የገጠር ትራንስፎርሜሽን ማምጣት እንደሚቻል ገልጸዋል።

የገጠር ትራንስፎርሜሽን ለማምጣት ቀዳሚው ጉዳይ ዘመናዊ ግብርናን መፍጠር አስፈላጊ ነው ብለዋል።

ከፍጆታ አልፎ ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚኾንና ለውጭ ገበያ የሚያቀርቡ አርሶ አደሮችን መፍጠር እንደሚገባም አመላክተዋል።

ሕልማችንን ማሳካት የሚያስችል ጸጋ አለን፣ መሬት፣ አየር፣ የማዕድን ሃብት፣ ትኩስ ጉልበት ያለው ወጣትና ሌሎች ሃብቶች አሉንም ብለዋል።

ኢንዱስትሪን መለማመድ፣ የሚጠይቀውን አቅም በመጠቀም ውጤታማ ሥራ መሥራት ያስፈልጋል ነው ያሉት።

ከተሜነትንና የከተማ ዕድገትን በአግባቡ መምራት እንደሚያስፈልግም ርዕሰ መስተዳድሩ አመላክተዋል።


 

ለቱሪዝም ዘርፉ ልዩ ትኩረት መስጠት እንደሚያስፈልግ ጠቁመው አንዱ የምጣኔ ሃብት ማሳለጫ አድርጎ መሥራት እንደሚገባም አመላክተዋል።

የቱሪዝም ሃብቶችን መለየት፣ መጠበቅ፣ ማልማትና ለጥቅም ማዋል እንደሚገባ ተናግረዋል።

የኢኮኖሚ ልማት ሥራዎችን በውጤታማነት እንዲመሩና ለመስኖ ልማት፣ ለእንስሳት መኖ ዝግጅት ትኩረት እንዲሰጥም አሳስበዋል።

የተፈጥሮ ሃብት ልማትን በተመለከተም ለማዕድን ሃብት ልማት ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንደሚገባ ተናግረዋል።

የንግድ ሥርዓቱን በተመለከተም ሕገ ወጥነትን፣ ኮንትሮባንድን መቆጣጠርና የገበያ ማዕከላትን መገንባት እንደሚገባ መግለጻቸውን አሚኮ ዘግቧል።

የሰው ሃብት ልማታችን ላይ እንሥራ ያሉት አቶ አረጋ ከበደ የትምህርት ተቋማት መገንባት እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።

ማህበረሰቡ የጤና መድኅን ተጠቃሚ እንዲሆን በትኩረት እንዲሠሩና የሴቶችን፣ የወጣቶችን፣ የሕጻናትንና የአካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ መሥራት እንደሚጠበቅም አመላክተዋል።

አገልግሎት አሰጣጥ ትኩረት እንዲሰጠው አሳስበው አገልጋዮች በጊዜ እና በቦታቸው ተገኝተው ለሕዝብ ተገቢውን አገልግሎት እንዲሰጡም አስገንዝበዋል።

የሪፎርም ሥራን በውጤታማነት እንዲተገብሩና ስምንቱ ሪጂዮፖሊታን ከተሞች መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ማስጀመርና ሌሎች ከተሞችም አስፈላጊውን ዝግጅት እንዲያደርጉ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም