የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ምርታማነት እመርታ የሥራ ዕድል ፈጠራና ክህሎት ሽግግርን እያሳለጠ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ምርታማነት እመርታ የሥራ ዕድል ፈጠራና ክህሎት ሽግግርን እያሳለጠ ነው
አዲስ አበባ፤ህዳር 18/2018(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ምርታማነት እመርታ የሥራ ዕድል ፈጠራና ክህሎት ሽግግርን እያሳለጠ መሆኑን ከፍተኛ የመንግስት ስራ ኃላፊዎች ገለጹ።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴዔታ ታረቀኝ ቡሉልታ እና የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴዔታ ሶሎሞን ሶካ የኢትዮጵያን የኢንዱስትሪ ምርታማነት፣ የሥራ ዕድል ፈጠራና ክህሎት ሽግግር በማስመልከት ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴዔታ ታረቀኝ ቡሉልታ፥ መንግስት አምስት የኢትዮጵያ የዕድገት ምሰሶ አድርጎ ከሰየማቸው ዘርፎች ውስጥ የኢንዱስትሪ ዘርፍ መዋቅራዊ ሽግግርን እያሳለጠ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የኢንዱስትሪ ዘርፍ ማነቆዎችን መፍትሔ በመስጠት ተዘግተው የነበሩ አምራች ኢንዱስትሪዎች ጭምር ወደማምረት የተመለሱበትን አቅም መፍጠር እንዳስቻለ ገልጸዋል።
በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ የተፈጠረው መነቃቃት አዳዲስ ኢንቨስትመንትን በመሳብ በተኪ ምርት፣ የሥራ ዕድል ፈጠራና ክህሎት ሽግግር ላይ አዎንታዊ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም ባለፉት አራት ዓመታት በአምራች ኢንዱስትሪ የተሰማሩ የሀገር ውስጥና የውጭ አልሚዎች ከ1 ነጥብ 18 ሚሊየን በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠራቸውን አስረድተዋል።
የአነስተኛ፣ መካከለኛና ከፍተኛ አምራቾችም የኢትዮጵያን የኢንዱስትሪ ምርታማነት በማሳደግ በወጪ ንግድ ሥርዓትም ተወዳዳሪ አቅም እየገነቡ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ተኪ ምርት ስትራቴጂም 96 የምርት አይነቶችን በመለየት ገቢ ምርቶችን መቀነስ ያስቻሉ ስኬታማ ውጤቶች እየተመዘገቡ መሆኑን አንስተዋል።
የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴዔታ ሰሎሞን ሶካ፥ የኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ተወዳዳሪነት አቅም በሥራ ዕድል ፈጠራና የክህሎት ሽግግር ወሳኝ ሚና እየተወጣ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ የተሰማሩ የሀገር ውስጥና የውጭ ኢንቨስትመንት አልሚዎችም በርካታ ዜጎችን የሥራ ዕድል ባለቤት እያደረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ለአብነትም ባለፉት አራት ወራት ውስጥ በአምራች ኢንዱስትሪዎች ውስጥ ከ218 ሺህ 113 በላይ ዜጎች የሥራ ዕድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ መደረጉን አስታውቀዋል።