ቀጥታ፡

የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትን የማረጋገጥ ግብን ለማሳካት ጥራትን ቀዳሚ ሀገራዊ አጀንዳ ማድረግ ይገባል

አዲስ አበባ፤ ህዳር 18/2018(ኢዜአ)፦የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትን የማረጋገጥ ግብን ለማሳካት ጥራትን ቀዳሚ ሀገራዊ አጀንዳ ማድረግ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ቴዎድሮስ መብራት ገለፁ።

የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ቴዎድሮስ መብራት ህዳር 20/2018 ዓ.ም የሚካሔደውን የጥራት ሽልማት መርኃ ግብር አስመልክቶ መግለጫ ሰጥተዋል።

ድርጅቱ ለጥራት ልዩ ትኩረት የሚሰጥ የሽልማት መርኃ ግብር በመዘርጋት በኢትዮጵያ የሚሰሩ አምራችና አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶችን ዓለም አቀፍ የተወዳዳሪነት ብቃት ማሳደግ ላይ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

ይህም ኢትዮጵያ ያላትን እምቅ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ሀብቶችን በአግባቡ ጥቅም ላይ በማዋል ምርትና ምርታማነትን ለማስፋት ጉልህ አስተዋጽኦ አለው ነው ያሉት።

ድርጅቱ በየዓመቱ የሚያካሂደው የጥራት ሽልማት ውድድር የተቋማትን የማምረት አቅም ለመጨመርና ጥራትን ለማስጠበቅ አስቻይ ሁኔታ እየፈጠረ ስለመሆኑም ጠቁመዋል።

ዘንድሮ በሚካሔደው 12ኛው የጥራት ሽልማት 65 ተቋማት የጥራት ውድድር ለማካሔድ መመዝገባቸውን አንስተዋል።

ከእነዚህ ውስጥ 63 ተቋማት እስከ ውድድሩ ፍፃሜ መጓዝ የቻሉ ሲሆን ባስመዘገቡት ውጤት ላይ በመመስረት የጥራት ተሸላሚ እንደሚሆኑ ዋና ስራ አስፈፃሚው ገልፀዋል።

ከዚህ ውስጥ 34 ተቋማት በአምራች ዘርፍ፣ 12ቱ ለትርፍ የተቋቋሙ አገልግሎት ሰጪዎች፣ 10 በጤና ዘርፍ፣ አምስት በአገልግሎት ዘርፍ፣ ሶስት በከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ እና አንድ ተቋም ደግሞ በኮንስትራክሽን ዘርፍ ተመዝግበው የተወዳደሩ ስለመሆናቸው አብራርተዋል።

ተቋማቱ የምርት ጥራትን በማስጠበቅ የኢትዮጵያን ተወዳዳሪነት ከፍ እንዲያደርጉ ይህ ሽልማት ትልቅ መነሳሳትን ይፈጥራል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም