የአደይ ፕሮግራም በግብርናው ዘርፍ በመሰማራት ተጠቃሚ እያደረገን ነው- ሴቶች እና ወጣቶች - ኢዜአ አማርኛ
የአደይ ፕሮግራም በግብርናው ዘርፍ በመሰማራት ተጠቃሚ እያደረገን ነው- ሴቶች እና ወጣቶች
አዲስ አበባ፤ህዳር 18/2018(ኢዜአ)፦ የአደይ ፕሮግራም በግብርናው ዘርፍ በመሰማራት በኢኮኖሚ ተጠቃሚ እያደረጋቸው መሆኑን በፕሮግራሙ የታቀፉ ሴቶችና ወጣቶች ተናገሩ፡፡
በአደይ ፕሮግራም እስካሁን 182 ሺህ ወጣቶችን በግብርናው ዘርፍ በኢንተርፕራይዝ በማደራጀት የስራ እድል እንደተፈጠረላቸው የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት አስታውቋል።
የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ለሴቶችና ለወጣቶች ሰፊ የሥራ ዕድል በመፍጠርና በኢኮኖሚ ራሳቸውን እንዲችሉ ማድረግን ያለመ አደይ የተሰኘ ፕሮግራም በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በመተግበር ላይ ነው።
በፕሮግራሙ የስራ እድል ከተፈጠረላቸው መካከል ከአንድ ዓመት በፊት 10 ሴቶች በማህበር በመደራጀት የመሰረቱት ቆሪቾ፣ ጂፋሬና ጓደኞቻቸው የዶሮ እርባታ ማኅበር ተጠቃሽ ነው።
የማህበሩ አባላት ስራ ከመጀመራቸው በፊት በግብርናው ዘርፍ ሰርቶ መለወጥ በሚቻልባቸው ዘዴዎች ላይ ስልጠና እንደተሰጣቸው ተናግረዋል።
በአደይ ፕሮግራም አማካይነት የዶሮ እርባታ ለመጀመር የዶሮ፣ የመኖና የመስሪያ ቦታ ድጋፍ እንደተደረገላቸውና ምቹ ሁኔታ እንደተፈጠረላቸው የማህበሩ አባል የሆነችው ወጣት ቆሪቾ ቦቼ ገልጻለች፡፡
የማህበሩ አባላት ምቹ ሁኔታውን በመጠቀም ወደ ዶሮ እርባታና እንቁላል ምርት በመግባት የእንቁላል ምርት ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግራለች።
ሌላኛዋ የማህበሩ አባል ጂፋሬ ገመቹ በማኅበር ተደራጅተን በዶሮ እርባታ ስራ እንድንጀምር በአደይ ፕሮግራም አማካኝነት 500 ዶሮዎችና የሶስት ወራት የዶሮ መኖ ድጋፍ ተደርጎልናል ብላለች ።
ከዚህ በፊት ስራ እንዳልነበራት አስታውሳ አሁን ላይ በፕሮግራሙ አማካይነት በማህበር በመደራጀት አምራች ዜጋ ሆኟለሁ ብላለች።
ሴና፣ አብዲሳና ጓደኞቻቸው የዶሮ እርባታ ማኅበር አባል የሆነው ወጣት አሽኖ እሸቱ ከዚህ በፊት ስራ እንዳልነበረው በማስታወስ በአደይ ፕሮግራም በግብርና ዘርፍ በመሰማራት ውጤታማ መሆን መቻሉን ተናግሯል ።
በፕሮግራሙ ድጋፍ አስር ሆነው በ500 ዶሮዎች በጀመሩት የዶሮ እርባታ ስኬታማ እየሆኑ እንደሚገኙ ገልጿል።
የአደይ ፕሮግራም ማንኛውንም ስራ በጋራና በትኩረት መስራት ከተቻለ ራስን መለወጥ እንደሚቻልና ስራ ፈጠራን በተመለከተ በጎ አመለካከት እንዲኖረው እንዳስቻለው አስረድቷል።
በኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት የአደይ ፕሮግራም ዳይሬክተር ኃይሌ ዴሬሳ በበኩላቸው ፕሮግራሙ በማስተር ካርድ ፋውንዴሽን ድጋፍ በመተግበር ላይ የሚገኝና የአምስት ዓመት ቆይታ ያለው ነው ብለዋል።
ፕሮግራሙ በኢትዮጵያ መተግበር ከጀመረ ሁለት ዓመት እንደተጠጋው ጠቅሰው መንግስት በግብርናው ዘርፍ የሴቶችንና የወጣቶችን የስራ አጥነት ችግር ለመቅረፍ በትኩረት እየሰራ ነው ብለዋል፡፡
በሁለት ዓመታት የትግበራ ጊዜውም 182 ሺህ ወጣቶችን በግብርናው ዘርፍ በኢንተርፕራይዝ በማደራጀት የስራ እድል እንደተፈጠረላቸው ተናግረዋል።
የስራ እድል ከተፈጠረላቸው መካከል 79 በመቶዎቹ ሴቶች መሆናቸውን ገልጸዋል።
በፕሮግራሙ አጠቃላይ የቆይታ ጊዜ ከ600 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ሴቶችና ወጣቶች የስራ እድል ለመፍጠር ግብ መቀመጡንም ጠቁመዋል፡፡