ኢትዮጵያ በቡድን-20 አባል አገሮች ጉባኤ ላይ ያደረገችው ተሳትፎ የላቀ ዲፕሎማሲ ስኬት የተመዘገበበት ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በቡድን-20 አባል አገሮች ጉባኤ ላይ ያደረገችው ተሳትፎ የላቀ ዲፕሎማሲ ስኬት የተመዘገበበት ነው
አዲስ አበባ፤ህዳር 18/2018(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ በቡድን-20 አባል አገሮች ጉባኤ ላይ ያደረገችው ተሳትፎ የላቀ ዲፕሎማሲ ስኬት የተመዘገበበት መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብያት ጌታቸው ገለጹ፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብያት ጌታቸው ዋና ዋና የዲፕሎማሲ ስራዎችን አስመልክተው ለመገናኛ ብዙሀን መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸው፥ ኢትዮጵያ የ2027 የኮፕ-32 (COP-32) ጉባዔን እንድታዘጋጅ መመረጧ የአየር ንብረት ለውጥን ለመግታት ለወሰደቻቸው እርምጃዎች እውቅና የሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።
ይህም የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ዓለም አቀፍ እውቅና እያገኘ ለመምጣቱ ትልቅ ማሳያ መሆኑንም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በኮሪደር ልማት፣ ንጹህ እና አረንጓዴ ከተሞችን ለማስፋፋት ለወሰደቻቸው ትላልቅ እርምጃዎች እውቅና የሰጠ ስለመሆኑም ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ ሁለተኛውን የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ በስኬት ማስተናገዷ ለመመረጧ ሌላኛው ምክንያት መሆኑንም ገልጸዋል።
በአጠቃላይ ኢትዮጵያ የኮፕ-32 አስተናጋጅ ሆና መመረጧ በዲፕሎማሲው መድረክ ያላት ተሰሚነት ወደ ላቀ ደረጃ እየተሸጋገረ ለመምጣቱ ትልቅ ማሳያ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ይህም የኢትዮጵያን በጎ ገጽታዎች ለማስተዋወቅና ለቱሪዝም ዕድገት ከፍተኛ ትርጉም ያለው መሆኑንም አስታውቀዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ (ዶ/ር) የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአየር ንብረት ጉባኤ (ኮፕ-32) ተወካይ ፕሬዝዳንት ሆነው መመረጣቸውንም ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በደቡብ አፍሪካ በተካሄደው የቡድን-20 ጉባኤ ላይ በመሳተፍ የዲፕሎማሲ ስኬት ማስመዝገቧን ጠቅሰዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በጉባኤው ባደረጉት ንግግር የአፍሪካን ሁነኛ አጀንዳዎችን ማንጸባረቃቸውንም አስታውሰዋል።
ከበርካታ ሀገራትና የተለያዩ ተቋማት መሪዎች ጋር ስኬታማ ውይይት ማድረጋቸውን ጠቁመው፤ በዚህም የሁለትዮሽ ግንኙነትን ማሳደግ መቻሉን ተናግረዋል።
በዚህም የልማት አጋርነት፣ ቀጣናዊና ዓለም አቀፍ ጉዳዮችን ጨምሮ በበርካታ ጉዳዮች ላይ መወያየታቸውን አንስተዋል።
ይህም የኢትዮጵያ የላቀ የዲፕሎማሲ ከፍታ የተገለጸበት መሆኑንም ጠቁመዋል።