ቀጥታ፡

የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን የህዝቦችን አብሮነት እያጠናከረ ነው

አዲስ አበባ፤ ህዳር 18/2018(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ባህልን ከማስተዋወቅ ባሻገር የህዝቦችን አብሮነት እያጠናከረ እንደሚገኝ የአዲስ አበባ ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባኤ ፋይዛ መሃመድ ገለጹ።

የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ 20ኛውን የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀንን ምክንያት በማድረግ የተማሪዎች የጥያቄና መልስ ውድድር እያካሄደ ይገኛል።

ከጥያቄና መልስ ውድድር ባሻገር በዓሉን ምክንያት በማድረግ የፓናል ውይይት የሚካሄድ ይሆናል።

የአዲስ አበባ ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባኤ ፋይዛ መሃመድ 20ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን "ዲሞክራሲያዊ መግባባት ለህብረ ብሔራዊ አንድነት" በሚል መሪ ሀሳብ በተለያዩ መርኃ ግብሮች በመከበር ላይ መሆኑን ጠቁመዋል።

የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ባህል ከማስተዋወቅ ባሻገር የህዝቦችን አብሮነት እያጠናከረ መሆኑን ገልጸው፤ ዜጎች በብሄራዊ ጉዳይ የጋራ ዓላማ እንዲኖራቸው አድርጓል ብለዋል።

የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ሃላፊ ዘላለም ሙላቱ (ዶ/ር) በበኩላቸው፥ የዘንድሮ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ሀገራችን ግዙፍ ልማቶችን ማሳካት በቻለችበት ወቅት መከበሩ ልዩ ደስታ እንደሚሰጥ ጠቅሰው፤ ለአብነትም የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን አንስተዋል።

በዓሉ የህዝቦችን ባህልና ወግ በማስተዋወቅ ለዲሞክራሲያዊ መግባባት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከተ ነው ብለዋል።

በተለይ የትምህርት ማህበረሰቡ የተማረና ብቁ የሆነ ዜጋን ለማፍራት ሚናቸውን ማጠናከር እንደሚገባ አፅንኦት ሰጥተዋል።

20ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል "ዲሞክራሲያዊ መግባባት ለህብረ ብሔራዊ አንድነት" በሚል መሪ ሃሳብ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አስተናጋጅነት ህዳር 29 ቀን 2018 ዓ.ም በሆሳዕና ከተማ ይከበራል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም