ቀጥታ፡

በምዕራብ ሸዋ ዞን በ16 ወረዳዎች አዳዲስ የመስኖ ፕሮጀክቶች ግንባታ እየተፋጠ ነው 

አምቦ፤ ህዳር 18/2018 (ኢዜአ)፦ በምዕራብ ሸዋ ዞን በ16 ወረዳዎች አዳዲስ የመስኖ ፕሮጀክቶች ግንባታ በመፋጠን ላይ መሆኑን የዞኑ መስኖ ልማት ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

በዞኑ የመስኖ ልማት ጽህፈት ቤት የኮንትራክተር አስተዳደርና የግንባታ ቁጥጥር የሥራ መሪ አቶ ዋቅጂራ ኦሊ ለኢዜአ እንደገለጹት፥ አርሶ አደሩን ከዝናብ ጥገኝነት በማላቀቅ በዓመት ሁለትና ከዚያ በላይ እንዲያመርት ለመስኖ ልማት ትኩረት ተሰጥቷል።

አርሶ አደሩ ያሉትን የውሀ አማራጮች በመጠቀም በመስኖ ልማት ምርታማነቱን በማሳደግ የምግብ ዋስትናውን እንዲያረጋግጥ የግብአትና የባለሙያ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑንም አንስተዋል።

የመስኖ ልማቱን ውጤታማ ለማድረግም በዞኑ 16 ወረዳዎች አዳዲስ የመስኖ ፕሮጀክቶች በግንባታ ሂደት ላይ እንደሚገኙም ተናግረዋል።

ግንባታቸው በመፋጠን ላይ የሚገኘው የመስኖ ፕሮጀክቶች በተያዘው ዓመት መጨረሻ ወደ ሥራ ለማስገባት ርብርብ እየተደረገ እንደሆነም አቶ ዋቅጂራ አመልክተዋል፡፡

በግንባታ ላይ የሚገኙት የመስኖ ፕሮጀክቶቹ ተጠናቀው ለአገልግሎት ሲበቁ 12 ሺህ 510 ሄክታር መሬት የማልማት አቅም አላቸው።

ፕሮጀክቶቹ ግንባታቸው እየተከናወነ ያለው ከመንግስትና ከህብረተሰቡ በተገኘ የገንዘብና የጉልበት ድጋፍ መሆኑን ጠቅሰው፣ ተጠናቀው ለአገልግሎት ሲበቁ 10ሺህ 272 አባውራዎችን ተጠቃሚ ያደርጋሉ ብለዋል።

ለመስኖ ፕሮጀክቶቹ ግንባታ ህብረተሰቡ በጉልበቱ፣ በቁሳቁስና በገንዘቡ ከ515 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት አስተዋጽኦ ማድረጉንም ተናግረዋል።

ፕሮጀክቶቹ  ተጠናቀው ወደ ስራ ሲገቡ ምርታማነትን ለማሳዳግ ካላቸው ፋይዳ ባለፈ በግንባታ ሂደታቸው ለበርካታ ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠራቸውንም ገልጸዋል።

በምዕራብ ሸዋ ዞን በዘንድሮ የበጋ ወራት 466 ሺህ750 ሄክታር መሬት በመስኖ እየለማ መሆኑን መዘገቡ ይታወሳል፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም