ቀጥታ፡

የምርምር ማዕከሉ የተሻሻሉ የሰብል ዝርያዎች የአርሶ አደሩን ምርታማነት ጨምረዋል

ወልቂጤ ፤ ህዳር 18/2018 (ኢዜአ)፦ የወልቂጤ ግብርና ምርምር ማዕከል ያቀረበላቸው የተሻሻሉ የሰብል ዝርያዎች ውጤታማ እያደረጋቸው መሆኑን በጉራጌ ዞን የጉመር እና ቸሃ ወረዳ አርሶ አደሮች ተናገሩ። 

የግብርና ምርምር ማዕከላት የአካባቢ ስነምህዳርን መሰረት ያደረጉ አዳዲስ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ለአርሶና አርብቶ አደሮች በማቅረብ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ረገድ ጉልህ ሚና እየተጫወቱ ነው።

በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የወልቂጤ ግብርና ምርምር ማዕከልም በጉራጌ ዞን የተሻሻሉ የሰብል ዝርያዎችን በማቅረብ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥና ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ እየሰራ ይገኛል።

በዞኑ የጉመር እና ቸሃ ወረዳ አርሶ አደሮች ለኢዜአ እንደገለጹት የምርምር ማዕከሉ በሽታን ተቋቁመው የተሻለ ምርት የሚሰጡ የሰብል ዝርያዎችን ከማቅረብ ባለፈ ሙያዊ ድጋፍ በማድረግ ውጤታማ እያደረጋቸው ነው።

ጉመር ወረዳ የአምዶም ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ብርሃኑ ሻፊ በአሲድ ከተጠቃ መሬታቸው በሄክታር ያገኙ የነበረው ምርት ከ10 ኩንታል እንደማይበልጥ አስታውሰዋል፡፡

የወልቂጤ ግብርና ምርምር ማዕከል ያቀረበላቸውን መስራች የተባለ የገብስ ምርጥ ዘር ተጠቅመው ማልማት ከጀመሩ ወዲህ በሄክታር 45 ኩንታል እያገኙ መሆናቸውንና ለአርሶ አደሮችም ምርጥ ዘር በተመጣጣኝ ዋጋ  እንደሚያቀርቡ ተናግረዋል፡፡  

በተጨማሪም የተሻሻሉ የግብርና አሰራሮችን በመተግባር የአተር፣ የባቄላና የድንች ምርጥ ዘር በማልማት ምርታማነታቸውን  እያሳደጉ መምጣታቸውን ተናግረዋል፡፡   

ሌላኛው አርሶ አደር ታሪኩ በስር በበኩላቸው የምርምር ማዕከሉ የተጎዳ መሬታቸውን በተቀናጀ ተፋሰስ ልማት በማልማትና በኖራ በማከም ለልማት እንዲውል ከማድረግ ባለፈ  ምርጥ ዘር እያቀረበላቸው መሆኑን ገልጸዋል።

ከዚህ ቀደም ድንች በሄክታር 50 ኩንታል ብቻ እንደሚያምርቱ የጠቀሱት አርሶ አደሩ ከማዕከሉ ያገኙትን ምርጥ ዘር ተጠቅመው እስከ 430 ኩንታል እንደሚያገኙ ተናግረዋል፡፡

ሰብሎችን በኩታ ገጠም በማልማት ከምርታቸው ተገቢውን ጥቅም እያገኙ በመሆኑ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸው ማደጉን ገልጸዋል፡፡

የተጎዳ መሬታቸውን በኖራ በማከም በመኸር አዝመራ ምርጥ ዘር ተጠቅመው ገብስ፣ ባቄለና አተር በኩታገጠም ማልማታቸውን የገለጹት ደግሞ የቸሃ ወረዳው  አርሶ አደር መሐመድ ቴኒ ናቸው፡፡

የምርምር ማዕከሉ ምርታማና በሽታ መቋቋም የሚችሉ የሰብል ዝርያዎችን እየቀረበላቸው መሆኑን ጠቅሰው በሄክታር 20 ኩንታል ብቻ የሚያገኙትን የስንዴ ምርት ወደ 45 ኩንታል ማሳደጋቸውን ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ ግብርና ኢንስቲትዩት የወልቂጤ ግብርና ምርምር ማዕከል ዳይሬክተርና ተመራማሪ ቤተል ነክር በበኩላቸው ማዕከሉ የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት፣ አሲዳማ አፈር በኖራ ማከም፣ አዳዲስ ዝርያ ማስተዋወቅና ማህበረሰብ አቀፍ የዘር ብዜት ላይ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል ።

በዘርፉ ከ118 በላይ የምርምር ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የጠቀሱት ሃላፊው የተሻሻሉ የበቆሎ፣ ጤፍ፣ ስንዴና የገብስ ዝርያዎችን በ218 ሄክታር ላይ በማልማት የተሻለ ዘር ለማግኘት እየተሰራ ነው ብለዋል ።

አክለውም ዞኑ በደጋማ ወረዳዎች በገብስ ልማት ያለውን ከፍተኛ አቅም በማጥናት “ጆቢራ” የሚባል አዲስ የገብስ ዝርያ ማስተዋወቁን ጠቅሰው፣ ማዕከሉ የአርሶ አደሩን ዘላቂ ተጠቃሚነትና ምርታማነትን ለማሳደግ አቅዶ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም