የኢትዮጵያ እና ኔዘርላንድስ የዲፕሎማሲ አጋርነት በንግድና ኢንቨስትመንት መስኮች ዕድገት እያስመዘገበ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ እና ኔዘርላንድስ የዲፕሎማሲ አጋርነት በንግድና ኢንቨስትመንት መስኮች ዕድገት እያስመዘገበ ነው
አዲስ አበባ፤ህዳር 18/2018(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያና ኔዘርላንድስ የዲፕሎማሲ አጋርነት በንግድና ኢንቨስትመንት መስኮች ዕድገት እያስመዘገበ መሆኑን በኢትዮጵያ የኔዘርላድስ ኤምባሲ ምክትል የሚሲዮን መሪ ፓውላ ሸናድለር ገለጹ።
በመጪው የፈረንጆቹ 2026 አዲስ ዓመትም በኢትዮጵያና ኔዘርላንድስ መካከል ከመቶ ዓመታት በፊት የተጀመረው የንግድ ግንኙነት እንደሚከበር ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ የኔዘርላድስ ኤምባሲ ምክትል የሚሲዮንና የልማት ኮርፖሬሽን መሪ ፓውላ ሸናድለር፤ ኢትዮጵያ እና ኔዘርላንድስ በጋራ ተጠቃሚነት መርህ የተመሠረተ ጠንካራ ወዳጅነት ያላቸው ሀገራት ናቸው ብለዋል።
የሁለቱ ሀገራት ታሪካዊ የዲፕሎማሲ ግንኙነትም በኢኮኖሚ ልማት የትብብር መስኮች ዕድገት እያስመዘገበ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ኔዘርላንድስ በኢትዮጵያ የምግብ ደኅንነት፣ የውሃ ሃብት አስተዳደርና ሌሎች የልማት መስኮች ያላትን አጋርነት እንደምታጠናክርም ተናግረዋል።
በዚህም በመጪው የፈረንጆቹ አዲስ ዓመት 2026 እ.አ.አ በ1926 የተጀመረው የሁለቱ ሀገራት የንግድ ዲፕሎማሲ ግንኙነታቸውን መቶኛ ዓመት እንደሚያከብሩ አስታውቀዋል።
በኢትዮጵያ የግብርና ምርቶች ላይ እሴቶችን በሚጨምሩ የንግድና ኢንቨስትመንት አማራጮች ላይ አንድ መቶ የሚሆኑ የኔዘርላንድስ አልሚ ድርጅቶች መሰማራታቸውን ተናግረዋል።
የኔዘርላንድስ የልማት ድርጅቶች የፍራፍሬና ሆርቲካልቸር የግብርና መስኮች የኢንቨስትመንት ተሳትፎም የዕውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግርን በማፋጠን ወሳኝ ሚና እየተወጡ ነው ብለዋል።
የኔዘርላንድስ አልሚዎች ኢንቨስትመንት የሀገራቱን የንግድ አጋርነት በማጎልበት ኢኮኖሚያዊ የዲፕሎማሲ ትብብርን እያጠናከረ እንደሚገኝ አስረድተዋል።