የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሰባተኛ ሳምንት ዛሬ ይጠናቀቃል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሰባተኛ ሳምንት ዛሬ ይጠናቀቃል
አዲስ አበባ፤ ሕዳር 18/2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሰባተኛ ሳምንት የመጨረሻ ቀን ውሎ ሶስት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።
ከቀኑ 7 ሰዓት ድሬዳዋ ከተማ ከምድረገነት ሽሬ በአዲስ አበባ ስታዲየም ይጫወታሉ።
ድሬዳዋ ከተማ በሊጉ ባደረጋቸው ስድስት ጨዋታዎች ሶስት ጊዜ ሲያሸንፍ ሁለት ጊዜ ተሸንፏል። በቀሪው አንድ ጨዋታ አቻ ተለያይቷል።
በጨዋታዎቹ አምስት ግቦችን ሲያስቆጥር ስድስት ግቦችን አስተናግዷል። ቡድኑ በ10 ነጥብ ስምንተኛ ደረጃን ይዟል።
ተጋጣሚው ምድረገነት ሽሬ በውድድር ዓመቱ ካካሄዳቸው ስድስት ጨዋታዎች መካከል ያሸነፈው አንድ ጊዜ ብቻ ነው። ሁለት ጊዜ ሲሸነፍ ሶስት ጊዜ ደግሞ ነጥብ ተጋርቷል። አራት ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ አምስት ግቦች ተቆጥረውበታል።
ምድረገነት ሽሬ በስድስት ነጥብ 15ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
በሌላኛው መርሃ ግብር መቀሌ 70 እንደርታ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከቀኑ 10 ሰዓት በአዲስ አበባ ስታዲየም ይጫወታሉ።
መቀሌ 70 እንደርታ በሊጉ እስከ አሁን ምንም ጨዋታ አላሸነፈም። ሶስት ጊዜ ሲሸነፍ በቀሪ ሶስት ጨዋታዎች አቻ ወጥቷል። በጨዋታዎቹ ስድስት ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ 10 ጎሎች ተቆጥረውበታል።
ቡድኑ በሶስት ነጥብ 18ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።
ተጋጣሚው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሊጉ ካደረጋቸው ስድስት ጨዋታዎች መካከል አንድ ጊዜ ሲያሸንፍ አንድ ጊዜ ተሸንፏል። አራት ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይቷል።
የ2016 ዓ.ም የሊጉ አሸናፊ በነዚህ ጨዋታዎች ስድስት ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ በተመሳሳይ ስድስት ግቦች ተቆጥረውበታል። ቡድኑ በሰባት ነጥብ 13ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ሀዲያ ሆሳዕና ከአርባምንጭ ከተማ ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ ይጫወታሉ።
ሀዲያ ሆሳዕና በውድድር ዓመቱ ካከናወናቸው ስድስት ጨዋታዎች አንድ ጊዜ ሲያሸንፍ ሁለት ጊዜ ሽንፈት አጋጥሞታል። ሶስት ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥቷል። አራት ግቦችን ከመረብ ጋር ሲያዋህድ ስድስት ግቦች ደግሞ አስተናግዷል።
ቡድኑ በስድስት ነጥብ 16ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ተጋጣሚው አርባምንጭ ከተማ በሊጉ እስከ አሁን ምንም ጨዋታ ማሸነፍ አልቻለም። ሶስት ጊዜ ሲሸነፍ በተመሳሳይ በሶስት ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርቷል። ሶስት ግቦችን ሲያስቆጥር ሰባት ግቦችን አስተናግዷል። በሶስት ነጥብ 19ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።