ቀጥታ፡

በተጠባቂው ጨዋታ አርሰናል ባየር ሙኒክን አሸነፈ

አዲስ አበባ፤ ህዳር 17/2018(ኢዜአ)፦ በተጠባቂው የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ መርሃ ግብር አርሰናል ባየር ሙኒክን 3 ለ 1 አሸንፏል።


 

ሊቨርፑል በበኩሉ ሽንፈት አስተናግዷል።

ማምሻውን በኤምሬትስ ስታዲየም በተካሄደው የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ ጨዋታ ዩሪየን ቲምበር በ22ኛው ደቂቃ ላይ ያስቆጠረው ግብ አርሰናልን መሪ አድርጓል።

የ17 ዓመቱ ሌናርት ካርል በ32ኛው ደቂቃ የባየር ሙኒክን የአቻነት ጎል ከመረብ ላይ አሳርፏል።

ኖኒ ማዱዌኬ በ69ኛው እና ጋብርኤል ማርቲኔሊ በ76ኛው ደቂቃ ያስቆጠሯቸው ግቦች የአርሰናልን አሸናፊነት አረጋግጠዋል።

ክለቦቹ በጨዋታው ላይ ለተመልካች አዝናኝ እንቅስቃሴ አሳይተዋል።

አርሰናል በ15 ነጥብ የሻምፒዮንስ ሊጉ መሪነትን ሲይዝ ባየር ሙኒክ በ12 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

አርሰናል በሻምፒዮንስ ሊጉ ለመጀመሪያ ጊዜ ግብ ሲቆጠርበት ባየር ሙኒክ የዘንድሮው የውድድር ዓመት ያለመሸነፍ ጉዞው ተገቷል።


 

በሌላኛው መርሃ ግብር የ15 ጊዜ የዋንጫው ባለቤት ሪያል ማድሪድ ከሜዳው ውጪ ኦሎምፒያኮስን 4 ለ 3 አሸንፏል።

ኪሊያን ምባፔ አራቱንም ግቦች ለሪያል ማድሪድ ከመረብ ላይ አሳርፏል።

ቺኩዊኒሆ፣ ሜህዲ ታህሬሚ እና አዩብ ኤልካቢ ለኦሎምፒያኮስ ግቦቹን አስቆጥረዋል።

የወቅቱ የውድድሩ ዋንጫ ባለቤት ፒኤስጂ ቶተንሃም ሆትስፐርስን 5 ለ 3 አሸንፏል።

ቪቲኒያ ሶስት ግቦችን በማስቆጠር ሀትሪክ ሲሰራ ፋቢያን ሩዊዝ እና ዊሊያን ፓቾ ቀሪዎቹን ግቦች ከመረብ ላይ አሳርፈዋል።

ለቶተንሃም ራንዳል ኮሎ ሙዋኒ ሁለት ግቦችን ሲያስቆጥር ሪቻርልሰን ቀሪዋን ጎል ከመረብ ጋር አገናኝቷል።

የፒኤስጂው ሉካስ ሄርናንዴዝ በ93ኛው ደቂቃ በቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል።

ሊቨርፑል በሜዳው በፒኤስቪ አይንድቨን 4 ለ 1 ተሸንፏል።

ኮሆሃይብ ድሩኤች ሁለት ግቦችን ሲያስቆጥር ጉስ ቲል በጨዋታ እና ኢቫን ፔሪሲች በፍጹም ቅጣት ምት ቀሪዎቹን ግቦች ከመረብ ላይ አሳርፈዋል።

ዶምኒክ ስቦዝላይ ለሊቨርፑል ብቸኛውን ጎል አስቆጥሯል።

በሌሎች ጨዋታዎች ኢንተር ሚላን አትሌቲኮ ማድሪድን 2 ለ 1

አትላንታ ኢንትራክት ፍራንክፈርትን፣ ስፖርቲንግ ሊዝበን ክለብ ብሩዥን በተመሳሳይ 3 ለ 0 አሸንፈዋል።

ዛሬ አስቀድመው በተካሄዱ ጨዋታዎች ኮፐንሀገን ካይራት አልማቲን 3 ለ 2 ሲያሸንፍ ፓፎስ ከሞናኮ ሁለት አቻ ተለያይተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም