ቀጥታ፡

አመራሩ በክልሉ የተመዘገቡ ውጤታማ የልማት ስራዎችን አጠናክሮ ለማስቀጠል ግንባር ቀደም ሊሆን ይገባል-ርእሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሀመድ

ጅግጅጋ፤ህዳር 17/2018 (ኢዜአ)፦በሶማሌ ክልል የተከናወኑ ውጤታማ የልማት ስራዎችን አጠናክሮ ለማስቀጠል አመራሩ ግንባር ቀደም መሆን እንዳለበት የክልሉ ርእሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሀመድ አስታወቁ።

"በመደመር መንግስት እይታ የዘርፎች እመርታ "በሚል ርዕስ በጅግጅጋ ከተማ የተሰጠው የክልሉ የከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች ስልጠና ዛሬ ተጠናቋል።

በሥልጠናው ማጠቃለያ ላይ የተገኙት የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ መሀመድ እንዳሉት፥ በለውጡ መንግስት የክልሉን ህዝብ ኑሮ የሚያሻሽሉ ሰፋፊ የልማት ኢንሼቲቮች ተከናውነዋል።

ከለውጡ በኋላ በግብርና፣በኢንዱስትሪ፣ በኢንቨስትመንት በተከናወኑ የልማት ሥራዎች ዘርፈ ብዙ ድሎች መመዝገባቸውን ጠቁመው አመራሩ የተመዘገቡ ውጤታማ የልማት ሥራዎች የበለጠ ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ግንባር ቀደም መሆን እንዳለበት አስገንዝበዋል ።

ስልጠናው የአመራሩን የመፈፀምና የማስፈፀም ብቃትና ጥራት በማሳደግ የተጀመሩ ለውጦችን ቀጣይነት ለማረጋገጥ አቅም የሚፈጥር ነው ብለዋል።

ስልጠናው በግብርና ገጠር ልማት፣በኢንዱስትሪ፣በከተማ ልማትና ቱሪዝም ጨምሮ በኢኮኖሚያዊ ዘርፎች ላይ አተኩሮ የተሰጠ መሆኑን አስታውቀዋል።

በስልጠናው በክልሉ በየደረጃው ያሉ ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች የተሳተፉ ሲሆን ከስልጠናው በተጓዳኝ የልማት ስራዎች የመስክ ጉብኝት ተካሂዷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም