ቀጥታ፡

የአዲስ አበባ ከተማ የልማት ሥራዎች በየአካባቢው የሚገኙ ፀጋዎችን በመለየት የብልጽግናን ጉዞ ማሳካት እንደሚቻል ያመላከቱ ናቸው

አዲስ አበባ፤ ህዳር 17/2018(ኢዜአ)፦ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተከናወኑ የልማት ሥራዎች በየአካባቢው የሚገኙ ፀጋዎችን በመለየት የብልፅግናን ጉዞ ማሳካት እንደሚቻል ያመላከቱ ናቸው ሲሉ የሁለተኛ ዙር ሰልጣኝ የፌዴራልና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የብልፅግና ፓርቲ አመራር አባላት ገለፁ።

"በመደመር መንግሥት እይታ የዘርፎች እመርታ" በሚል መሪ ሀሳብ የሁለተኛ ዙር ስልጠና ሲከታተሉ የቆዩ የፌዴራል እና የአዲስ አበባ ከተማ የብልፅግና ፓርቲ አመራር አባላት በከተማው አስተዳደር የተከናወኑ የልማት ስራዎችን ጎብኝተዋል።

በጉብኝታቸው የኮሪደር እና የወንዝ ዳርቻ ልማት ስራዎች፣ የዘውዲቱ ሆስፒታል ማስፋፊያ፣ የሳይንስ ሙዚየም፣ የአራዳ ፓርክ፣ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት፣ አሻራ የጋራ መኖሪያ መንደርና ላፍቶ ቁጥር ሁለት ሁለገብ የገበያ ማዕከልን ተዘዋውረው ተመልክተዋል።

ሰልጣኞቹ በጉብኝታቸው የተመለከቷቸው ልማቶች በየአካባቢው ያሉ ፀጋዎችን በመለየት የብልጽግናን ጉዞ ማሳካት እንደሚቻል ያረጋግጣል ብለዋል።

ከጉብኝቱ ተሳታፊዎች መካከል አስተያየታቸውን የሰጡን አቶ ደመረ አሰፍ እንደሚናገሩት፤ የወሰዱት ስልጠና ለቀጣይ ስራቸው ትልቅ አቅም የሚሰጥ ነው።

ከስልጠናው ጋር በተያያዘ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተመለከቱት የልማት ስራዎች የብልጽግናን ጉዞ ማሳካት እንደሚቻል የታየበት ነው ብለዋል።

ከሰልጣኝ አመራር አባላት መካከል አቶ ጥላሁን ቶላ በበኩላቸው፤ የዕይታ ለውጥ ወደ ተሻለ ደረጃ ማሸጋገር እንደሚቻል በጉብኝታቸው ተረድተዋል።

በከተማዋ እየተሰሩ ያሉ የልማት ፕሮጀክቶች አፈፃፀም ለሌሎች በአርዓያነት የሚጠቀሱ መሆናቸውን ነው ተስፋዬ ኤባ (ዶ/ር) የገለጹት።

ፕሮጀክቶችን በታቀደላቸው ጊዜ ማጠናቀቅ መቻሉ የሀገርን እድገት በአጭር ጊዜ ውስጥ ማረጋገጥ እንደሚችል የሚያሳይ መሆኑንም አስረድተዋል።

በከተማዋ የተከናወኑትን የልማት ስራዎች ከቃል ወደ ተግባር የሚለውን መርህ በተጨባጭ የተመለከትንበት ነው ያሉት ደግሞ አቶ ጥላሁን ካሳ ናቸው። 

ሌላው ከሰልጣኝ አመራር አባላት መካከል ወይዘሮ ይርጋለም እንየው እንደተናገሩት፤ በጉብኝቱ የታዩት ስኬቶች በሁሉም አካባቢ የሚገኙ ሀብቶችን በአግባቡ በመጠቀም ብልጽግናን ማምጣት እንደሚቻል ያሳያል።

ሰልጣኝ አመራር አባል አቶ አብዲሳ ተስፋዬ በበኩላቸው፤ የልማት ስራዎቹ የብልጽግናን ጉዞ ለማፋጠን የአመራርን ቁርጠኝነት እንደሚያጠናክር ገልጸዋል። 
 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም