በክልሉ የሕብረተሰቡን የልማት ጥያቄ መመለስ የሚያስችሉ የግንባታ ተግባራት ተጠናክረው ቀጥለዋል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የሕብረተሰቡን የልማት ጥያቄ መመለስ የሚያስችሉ የግንባታ ተግባራት ተጠናክረው ቀጥለዋል
ነቀምቴ፤ሕዳር 17/2018(ኢዜአ)፡- በአሮሚያ ክልል የሕብረተሰቡን የልማት ጥያቄ መመለስ የሚያስችሉ የተለያዩ የግንባታ ተግባራት ተጠናከረው መቀጠላቸውን በክልሉ ምክትል ፕሬዚዳንት ማዕረግ የከተማ ክላስተር አስተባባሪ አቶ መስፍን መላኩ ገለጹ።
’’በመደመር መንግስት እይታ የዘርፎች እመርታ’’ በሚል መሪ ሃሳብ በነቀምቴ ክላስተር ሲሰለጥኑ የቆዩ የኦሮሚያ ክልል ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች በከተማዋ የተለያዩ የልማት እንቅስቃሴዎችን ጕብኝተዋል።
በጉብኝቱ ወቅት በኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት ማዕረግ የከተማ ክላስተር አስተባባሪ አቶ መስፍን መላኩ እንደተናገሩት፥ በክልሉ የሰፈነውን ሰላም በማፅናት ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋና የከተሞች የኮሪደር ልማትን ጨምሮ ሌሎችም የልማት ተግባራት ሲከናወኑ ቆይተዋል።
በዚህም ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት መቻሉን አንስተዋል።
በአሁኑ ወቅትም የክልሉ መንግስት የሕብረተሰብ የልማት ጥያቄ ለመመለስ የመንገድ ፣ የኢንደስትሪያል ፓርኮች፣ የአውሮፕላን ማረፊያና ሌሎችንም የግንባታ ተግባራት አጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል።
ነዋሪዎችም ሰላምን በመጠበቅ ልማትን ለማፋጠን በሚደረገው ጥረት በንቃት እየተሳተፉ መሆኑን አንስተዋል።
በልማቱ ጉብኝቱ ላይ የተሳተፉ አመራሮች፤መንግስት የሕዝብ የልማት ተሳትፎ በማሳደግ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነቱን ለማሳደግ እያከናወናቸው ያሉት ተግበራት ተጨባጭ ለውጥ እያመጡ እንደሆኑ መመልከታቸውን ገልጸዋል።
ከአመራሮቹም መካከል ወይዘሮ ቢቂልቱ አገሳ ፤ከስልጠናው ሀገራዊና ክልላዊ ጉዳዮችን ይበልጥ የተረዱበትና ሕዝብን ለማገልገል ተጨማሪ አቅም የፈጠሩበት መሆኑን ተናግረዋል።
ከስልጠናው ጎን ለጐን በነቀምቴ ከተማ የተሰሩ የልማት ተግበራት መመልከታቸውም ለቀጣይ ስራቸው ልምድ መቅሰማቸውን አክለዋል።
በነቀምቴ የተከናወኑ የኮሪደር ልማትና ሌሎች ግንባታዎች በፍጥነት መጠናቀቅ መንግስት ፕሮጀክቶችን በተያዘላቸው ጊዜ የመጨረስ አቅም መፍጠሩን ያረጋገጥንበት ነው ብለዋል።
ሌላኛው ሰልጣኝ አቶ ደረጄ ወርቁ፤ በነቀምቴ ከተማ የተገነቡና በግንባታ ላይ ያሉ ፕሮጀክቶች የስራ እድል በመፍጠር እያበረከቱት ያለው አስተዋጽኦ የሚበረታታ መሆኑን ገልጸዋል።
በጉብኝታቸውም የአካባቢው የልማት አቅም ወደ ውጤት ለመቀየር የሕዝብና መንግስት ትብብርን ማላቅ እንደሚገባ መረዳታቸውን ተናግረዋል።
በተለይም ከተማዋን ውብ፣ ሳቢ እና ዘመናዊ ለማድረግ የተጀመረው የኮሪደር ልማት ለኑሮና ለኢንቨስትመንት ተመራጭ እንዳደረጋት መመልከታቸውን አረጋግጠዋል።