በመንግስት እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎች ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት የሚያስችሉ ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
በመንግስት እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎች ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት የሚያስችሉ ናቸው
ባህር ዳር፤ህዳር 17/2018 (ኢዜአ)፦መንግስት ለህዝብ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት እያከናወናቸው ያሉ የልማት ሥራዎች ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት የሚያስችሉ ናቸው ሲሉ በባህር ዳር ከተማ የተሳተፉ ሰልጣኝ አመራሮች ገለጹ።
"በመደመር መንግስት እይታ የዘርፎች እመርታ" በሚል መሪ ሀሳብ ስልጠና ሲከታተሉ የቆዩ የአማራ ክልል ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች በባሕር ዳር ከተማ የተከናወኑ የልማት ሥራዎችን ጎብኝተዋል።
አመራሮቹ በቱሪዝም፣በከተማ ልማት፣ በግብርናና ገጠር ልማት እንዲሁም በማዕድን ዘርፎች ላይ ያተኮሩ ስልጠናዎችን ሲከታተሉ ቆይተዋል።
አመራሮቹ የስልጠናው መጠናቀቅን ተከትሎ በባህር ዳር ከተማ በተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎችን ዛሬ ጎብኝተዋል።
በጉብኝቱ ላይ ከተሳተፉት አመራሮች መካከል ኮከቤ ሰይድ ለኢዜአ እንደገለጹት፥ጉብኝቱ በንድፈ ሃሳብ ስልጠናው የተነገራቸው በተግባር እየተከናወነ መሆኑን ያረጋገጡበት ነው።
በባህር ዳር ከተማ እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት ሥራ የህዝቡን ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ ባለፈ ከተማውን ፅዱ፣ ውብና ለኑሮ ምቹ ማድረግ አስችሏል ብለዋል።
በከተማው በኢንዱስትሪ ማስፋፋት፣ በቱሪዝም ልማትና በሌሎች የኢኮኖሚ ዘርፎች እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎች በተሞክሮነት የሚወሰዱ መሆናቸውን ገልፀዋል።
በስልጠናው በንድፈ ሃሳብ ያየነውን በተግባር እየተከናወነ መሆኑን አይተናል ያሉት ደግሞ ሌላው ተሳታፊ እንድሪስ አብዱ ናቸው።
በለውጡ መንግስት በተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎች የህዝብን ተጠቃሚነት እያሳደጉ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በባህር ዳር ከተማ እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት ከተማዋ የበለጠ ጎልታ እንድትወጣ ያደረገና ለሌሎችም ልምድ እንደሚሆን አመልክተዋል።
ሌላው የጉብኝቱ ተሳታፊ አብዱልናስር ጀማል በበኩላቸው፥ ባህር ዳር ከተማ በኢንዱስትሪ፣ በቱሪዝምና መሰል ዘርፎች ተጨባጭ ለውጥ እንዳለ በተግባር አይተናል ብለዋል።
መንግስት በሁሉም ዘርፎች እያከናወናቸው ያሉ የልማት ሥራዎች የህዝብን ተጠቃሚነት ብሎም ኢኮኖሚያዊ እድገትን እያረጋገጡ ስለመሆኑ ማሳያ ናቸው ብለዋል።
መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የተቀላጠፈ አገልግሎት በመስጠት የህዝብን እንግልት እየቀነሰ መሆኑንም ማየት ችለናል ሲሉ ገልጸዋል።
የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው በበኩላቸው፥ ባህር ዳር የቱሪዝም፣የመዝናኛ፣ የኢንዱስትሪ፣ የኢንቨስትመንትና የግብርና ከተማ መሆኗን ማረጋገጥ እየተቻለ ነው።
ባህር ዳርን ስማርት ከተማ ለማድረግ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ጠቁመው በተለይም በኮሪደር ልማት አርአያ የሚሆኑ ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛል ብልዋል።
በከተማው በአራት የኢንዱስትሪ መንደር ከ670 በላይ ባለሃብቶች መሬት መውሰዳቸውን ጠቁመው፥ ከባለሀብቶቹ ውስጥ 235 የሚሆኑት የማምረት ደረጃ ላይ ናቸው፤ ተኪ ምርትም እያቀረቡ ነው ብለዋል።
በዚህም የለውጡ መንግስት በሁሉም ዘርፍ እምርታ እናመጣለን ብሎ እያደረገ ያለው ርብርብ በተጨባጭ ለውጥ እየመጣ ነው ብለዋል።