ፈረንሣይ ከኢትዮጵያ ጋር በወታደራዊ መስክ የምታደርገውን ትብብር ታጠናክራለች - የፈረንሣይ ምድር ጦር አዛዥ ጄኔራል ፒየር ሺል - ኢዜአ አማርኛ
ፈረንሣይ ከኢትዮጵያ ጋር በወታደራዊ መስክ የምታደርገውን ትብብር ታጠናክራለች - የፈረንሣይ ምድር ጦር አዛዥ ጄኔራል ፒየር ሺል
አዲስ አበባ፤ ሕዳር 17/2018(ኢዜአ)፦ፈረንሣይ ከኢትዮጵያ ጋር በወታደራዊ መስክ ያላትን ትብብር የበለጠ በማጠናከር ለመሥራት ዝግጁ መሆኗን የፈረንሣይ ምድር ጦር አዛዥ ጄኔራል ፒየር ሺል ገለፁ።
በጄነራል ፒየር ሺል የተመራ የፈረንሣይ ወታደራዊ ልዑክ ከኢፌዴሪ መከላከያ አመራሮች ጋር በሁለቱ ሃገራት ወታደራዊ ትብብርና በሰላም ማስከበር ኦፕሬሽኖች ዙሪያ ውይይት አድርጓል።
ወታደራዊ ትብብሩ የሁለቱ ሀገራት መሪዎች ያደረጓቸውን ስምምነቶች ተከትሎ የተደረገ እንደሆነም ነው የተመላከተው።
ኢትዮጵያ የቀጣናውን ሠላም ለማረጋገጥ በምታደርገው ጥረት መደሰታቸውን የገለፁት ጄኔራል ፒየር ሺል በቀጣይነት አስፈላጊ በሆኑ ጉዳዮች በሁለትዮሽ ትብብር እንደሚሠሩም ገልፀዋል።
ጄነራል ፒየር ሺል በሠላም ማስከበር ተልዕኮ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ተሣትፎ አስፈላጊ ነው ተጠናክሮ መቀጠልም አለበት ብለዋል።
ፈረንሣይ ለጋራ ተጠቃሚነት በወታደራዊ ቁሳቁስ ድጋፍ፣ በሠው ኃይል ሥልጠና እና ያልተቆራረጠ ወታደራዊ ትብብር ለማድረግ ዝግጁ መሆኗንም አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ ጦር በአፍሪካ ጠንካራ ኃይል መሆኑን የገለፁት የኢፌዴሪ መከላከያ ትምህርትና ሥልጠና ዋና መምሪያ ኃላፊ ጄኔራል ይመር መኮንን ዘመኑ በሚጠይቀው ወታደራዊ ቴክኖሎጂ ታግዞ ግዳጅ ለመወጣት ከፈረንሣይ ጋር በትብብር እንሠራለን ብለዋል።
ጄኔራል ይመር መኮንን ከፈረንሣይ ጋር የረጅም ዓመታት ወታደራዊ ግንኙነት አለን ይህንኑ የቆየ ወዳጅነታችንን በተለያዩ ወታደራዊ ዘርፎች አጠናክረን መቀጠል እንፈልጋለን ብለዋል።
በውይይቱ የኢትዮጵያ መከላከያ ጄኔራል መኮንኖች ከፈረንሣይ መከላከያ ጋር መሠራት ባለባቸው ወታደራዊ መስኮች ዙሪያ ሃሳብ ተለዋውጠዋል።
ሁለቱ ሀገራት በወታደራዊ መስክ ያላቸው ዳራ፣ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ሽብርተኝነትን ለመዋጋት እያከናወናቸው ስላለው ተግባራት በመከላከያ ሠላም ማስከበር ማዕከል ገለፃ ተደርጓል።
ጄኔራል ፒየር ሺል በነገው ዕለትም ከጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ጋር ተገናኝተው እንደሚመክሩና ጉብኝት እንደሚያደርጉ ኢዜአ ከመከላከያ ሰራዊት ኦንላይን ሚዲያ ያገኘው መረጃ ያመለክታል።