ስታርትአፖች ለሀገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ምቹ ምህዳር እየተፈጠረ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ስታርትአፖች ለሀገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ምቹ ምህዳር እየተፈጠረ ነው
አዲስ አበባ፤ህዳር 17/2018(ኢዜአ)፦ስታርትአፖች ለሀገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ምቹ ምህዳር እየተፈጠረ መሆኑን የኢንተርፕርነርሽፕ ልማት ኢንስቲትዩት ገለፀ።
ዓለምአቀፍ የኢንተርፕርነር ሳምንትን አስመልክቶ ስታርታፖችና የኢንተርፕረነርስ ፋይናንስ ላይ ያተኮረ የፓናል ውይይት በአዲስ አበባ ተካሂዷል።
የኢንተርፕርነርሽፕ ልማት ኢንስቲትዩት የቢዝነስ ዴቨሎፕመንት ሰርቪስ ፕሮግራም ስራ አስኪያጅ ዮናታን ይልማ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ስታርትአፖች ያላቸውን አቅም በበቂ ሁኔታ እንዲጠቀሙ የተለያዩ ድጋፎች እየተደረጉ ነው።
ጀማሪ ስታርትአፖች ትክክለኛ ምርትና አገልግሎት እንዲያቀርቡ የአቅም ግንባታ ድጋፍ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን አመልክተዋል።
በተለይም የፈጠራ ሃሳብና አቅም ያላቸው ስታርትአፖች የፋይናንስ ችግር እንዳይገጥማቸው በማገዝ ለኢኮኖሚ ዕድገት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ማድረግ ይገባል ብለዋል።
በክልል የሚገኙ ስታርትአፖችን በማወዳደርና የአቅም ግንባታ ስልጠና በመስጠት ዘርፉን እንዲያሳድጉ እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል።
ስታርትአፖችና ስራ ፈጣሪዎች የገንዘብ ምንጭ የሚያገኙበትንና ራሳቸውን ብቁ የሚያደርጉበትን ስልጠና ከመስጠት ባለፈ የገበያ ትስስር እንዲፈጥሩ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ የሰነድ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ ባለሙያ የሆኑት ዮሃንስ እስጢፋኖስ በሀገራችን የሰነድ መዋዕለ ንዋይ ገበያ መጀመር ለስታርትአፖችና ስራ ፈጣሪዎች ትልቅ እድል ይዞ መምጣቱን ተናግረዋል።
በዋናነት የስታርትአፖችን የፋይናንስ እጥረት በመፍታት በሀገር ኢኮኖሚ ውስጥ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ የሚያስችል መሆኑን ጠቁመዋል።
ገበያው ስታርትአፖች የራሳቸውን ሃብት እንዲያፈሩ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ጠቁመዋል።
በፓናል ውይይቱ ከተሳተፉ የስታርት አፕ ተወካዮች መካከል አቶ ሚሊዮን ግርማይ በበኩላቸው፤ በስታርታፕ ዘርፍ ከሚገጥሙ ተግዳሮች አንዱ በምስረታ ወቅት በቂ ፋይናንስ አለማግኘት ነው ብለዋል።
ስታርትአፖችን ለመደገፍና አቅማቸውን ለማሳደግ መንግስት እያከናወነ ያለው ተግባር የሚበረታታ መሆኑን ተናግረዋል።
በተለይም ከወለድ ነፃ እንዲሁም ንብረት ሳያሲዙ ገንዘብ እንዲያገኙ የተጀመሩ ስራዎች ተግባራዊ ሲደረጉ በዘርፉ ትልቅ ለውጥ እንደሚመጣ ተናግረዋል።