ኢትዮጵያ ፍትሕን በማስፈን የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ሕጎችን በማውጣት በቀጣናው የመሪነት ሚና አላት - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ፍትሕን በማስፈን የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ሕጎችን በማውጣት በቀጣናው የመሪነት ሚና አላት
አዲስ አበባ፤ ህዳር 17/2018(ኢዜአ)፦ በምሥራቅ አፍሪካ ፍትሕን በማስፈን የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ኢትዮጵያ ሕጎችን በማውጣት የመሪነት ሚና ያላት ሀገር መሆኗን የምሥራቅ አፍሪካ የሕግ ማህበረሰብ ፕሬዝዳንት ረመዳን አቡበከር ገለጹ፡፡
የምሥራቅ አፍሪካ የሕግ ማህበረሰብ ከፍትሕ ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ፈዴራል ጠበቆች ማህበር ጋር በመተባበር 30ኛ ዓመት የምሥረታና ዓመታዊ ጉባኤውን በመጪው ዓርብ በአፍሪካ ህብረት ያካሂዳል፡፡
በዚህ ጉባኤ የቀጣናውና የሌሎችም ሀገራት ተጋባዥ የህግ ባለሙያዎች የሚሳተፉበት የውይይት መድረክ በስካይ ላይ ሆቴል እየተካሄደ ነው፡፡
የምሥራቅ አፍሪካ የሕግ ማህበረሰብ ፕሬዝዳንት ረመዳን አቡበከር በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ ጉባኤው የአፍሪካ ህብረትና የሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት መገኛ በሆነችው ኢትዮጵያ መካሄዱ ዘርፈ ብዙ ጥቅም አለው፡፡
ኢትዮጵያ የምሥራቅ አፍሪካ የሕግ ማህበረሰብ አባልነትን የተቀላቀለችው ባለፈው ዓመት እንደነበር አስታውሰው፤ በቀጣናው ፍትሕን በማስፈን የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ወሳኝ ሀገር መሆኗን ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ ለፍትህና የሕግ የበላይነት መረጋገጥ መሰረታዊ እና ሌሎች ሀገራት የሚማሩባቸው ህጎችን በማውጣት የመሪነት ሚና ያላት ሀገር ነች ብለዋል፡፡
የምሥራቅ አፍሪካ የሕግ ማህበረሰብ ሀገራት ትብብራቸውን በማጠናከር ፍትሕን የማስፈን ግብ እንዳለው ገልጸው፤ በቀጣናው ጠንካራ የፍትሕ ተቋማትን መገንባት እንደሚያስችል ተናግረዋል፡፡
በቀጣናው የተለያዩ ክህሎት እውቀትና አቅም ያላቸው የህግ ባለሙያዎችና ማህበራት እንዳሉ በመጥቀስ፤ ሕጎችን ገቢራዊ ለማደረግ የመማማሪያ መድረክ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ፌደራል ጠበቆች ማህበር ፕሬዝዳንት ቴዎድሮስ ጌታቸው በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ የበርካታ ተቋማት መገኛ የፓን አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ መስራች መሆኗን ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያ የተደረገው ሀገራዊ ሪፎርም የፌደራል ጥብቅና አገልግሎት ፍቃድ አሰጣጥ እና አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 1249/2013 መጽደቁን በማንሳት፤ የኢትዮጵያ ፌደራል ጠበቆች ማህበር ከአምስቱ መሰረታዊ የፍትህ ተቋማት አንዱ እንዲሆን አስችሎታል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ የምሥራቅ አፍሪካ የሕግ ማህበረሰብ አባል መሆን በቀጣናው ፍትሕን ለማስፈንና የህግ የበላይነት ለማረጋገጥ የሚኖራትን ሚና ከፍ እንደሚያደርገው ተናግረዋል፡፡
የምሥራቅ አፍሪካ የሕግ ማህበረሰብ ጉባኤ በሀገራት የሕግ ባለሙያዎችና ተቋማት መካከል የተሳለጠ የመረጃ ልውውጥ በመፍጠር ቀጣናዊ ትብብርን ያሳድጋል ብለዋል፡፡