ቀጥታ፡

ረቂቅ አዋጁ የግብርና ዘርፉን ለማሸጋገርና የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ጉልህ ፋይዳ ይኖረዋል

አዲስ አበባ፤ ህዳር 17/2018(ኢዜአ)፦ የዕፅዋት ጥበቃና ኳራንቲን ረቂቅ አዋጅ የግብርና ዘርፉን ለማሸጋገርና የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ጉልህ ፋየዳ እንደሚኖረው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ገለጸ።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በግብርና ሚኒስቴር የዕፅዋት ጥበቃና ኳራንታይን ረቂቅ አዋጅ ላይ የሕዝብና የባለድርሻ አካላት የምክክር መድረክ አካሂዷል።

በግብርና ሚኒስቴር የዕፅዋት ጥበቃና ቁጥጥር ጉዳዮች አማካሪ ተክሉ ባይሳ፤ በዕፅዋትና እንስሳት ሃብት የሚከሰት ተባይና በሽታ ቀላል የማይባል ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና አካባቢያዊ ተፅዕኖ አላቸው ብለዋል።

በዕፅዋትና እንስሳት ላይ የሚደርሱ የተባይና በሽታዎችን ለመከላከልም የዕፅዋት ጥበቃና የእንስሳት ማቆያ ማዕከል ረቂቅ አዋጅ በርካታ ሂደቶችን አልፎ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

የዕፅዋት ጥበቃና ኳራንታይን ረቂቅ አዋጅ ስራ ላይ ሲውል በዕፅዋትና እንስሳት ሃብት ላይ የሚደርሱ ጉዳቶችን አፋጣኝ የመፍትሔ እርምጃ ለመውሰድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አብራርተዋል።

በዚህም ረቂቅ አዋጁ ዘመናዊ የተባይና በሽታ መከላከያና መቆጣጠሪያ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም በመረጃና ጥናት ላይ የተመሰረተ የምርታማነት ሥርዓት ለመፍጠር እንደሚያግዝ አስረድተዋል።

የውይይቱ ተሳታፊ ባለድርሻ አካላትም፤ በረቂቅ አዋጁ ላይ የዕፅዋትና እንስሳት ደኅንነትና ቁጥጥር፣ የሕግ ተጠያቂነትና ዓለም አቀፍ የሰብል ጥበቃ መርሆችን መካተት እንደሚኖርባቸው አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወንዳለ ሀብታሙ(ዶ/ር)፤ ከዚህ ቀደም የዕፅዋትና እንስሳት ምርታማነትን ለማስጠበቅ ለ55 ዓመታት ያህል ያገለገለ ሕግ በስራ ላይ መኖሩን አስታውሰዋል።

በዕፅዋት ጥበቃና ኳራንታይን ረቂቅ አዋጅ በምርምር የተደገፉ የተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎች መጠቀም በሚያስችል መልኩ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ጭምር ተካተውበት መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

በቀጣይም ባለድርሻ አካላት ለረቂቅ አዋጁ ግብዓት እንዲሆኑ ያቀረቧቸውን ምክረ ሃሳቦች ከከፍተኛ ትምህርትና የምርምር ተቋማት ጋር ጭምር በቅንጅት እንደሚሰራ ተናግረዋል።

የግብርና ሚኒስቴር ዴኤታ መለሰ መኮንን (ዶ/ር)፤ የኢትዮጵያን የግብርና መዋቅራዊ ሽግግር በማሳለጥ ምርታማነትን ለማስቀጠል በልዩ ትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።

የዕፅዋት ጥበቃና ኳራንታይን ረቂቅ አዋጅም በዕፅዋትና እንስሳት ላይ የሚያጋጥም ተባይና በሽታን በተሻለ አሰራር በመምራት የግብርና ምርት ጥራትና ደኅንነትን ለማስጠበቅ ወሳኝ ሚና እንደሚኖረው ገልጸዋል።

በግብርናው መስክ የኢትዮጵያን የምግብ ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ ከሚደረገው ጥረት ባሻገር ወደ ውጭ የሚላክ ምርት በመጠንና በጥራት ለማስጠበቅ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ሰለሞን ላሊ ረቂቅ አዋጁ የዕጽዋት ጥበቃ እና ኳራንታይን ስራዎችን ለማጠናከርና ምርታማነትን ለማሻሻል ጉልህ ጠቀሜታ ይኖረዋል ብለዋል። 

የግብርና ዘርፉን ለማሸጋገርና የምግብ ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ ጠቀሜታው የላቀ መሆኑን ጠቅሰዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም