ቀጥታ፡

የአፋር ክልል የትምህርት ቤቶችን ምገባ በራስ አቅም ለመሸፈን የጀመራቸው የሰብል ልማት ተግባራት ተሞክሮ የሚወሰድበት ነው

ሰመራ፤ሕዳር 17/2018(ኢዜአ)፡-የአፋር ክልል የትምህርት ቤቶችን ምገባ በራስ አቅም ለመሸፈን የጀመራቸው የሰብል ልማት ተግባራት ተሞክሮ የሚወሰድበትና የሚበረታታ መሆኑን የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።

የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ አየለች እሼቴ የትምህርት ቤቶች ምገባ ሀገር በቀል አሳቤ መሆኑን ጠቅሰው፤ ተማሪዎችን በራስ ከቅም ለመመገብ የሚያስችሉ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን በአፋር ክልል ምልከታችን ለማየት ችለናል ብለዋል።

በአፋር ክልል ትምህርት ቤቶች ለተማሪዎች ምገባ እንዲሆን ታስቦ በዱብቲ ወረዳ 100 ሄክታር መሬት ላይ ሰብል እየለማ መሆኑን ገልጸዋል።

ሚኒስትር ዴኤታዋ አየለች እሼቴ ልማቱን በዱብቲ ወረዳ በመገኘት ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።

ሚኒስትር ዴኤታዋ በወቅቱ እንደገለጹት፤ክልሉ የትምህርት ቤቶችን ምገባ በራስ አቅም ለመሸፈን የጀመራቸው የሰብል ልማት ተግባራት ተሞክሮ የሚወሰድበትና የሚበረታታ ነው።

መሰል የልማት ስራም በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች እስከ ስምንተኛ ክፍል ያሉት ትምህርት ቤቶች ተማሪዎቻቸውን በሙሉ መመገብ እንዲችሉ የወጣውን ዕቅድ ለማሳካትም የሚያግዝ መሆኑን ተናግረዋል።

የክልሉ መንግስትም በጀት መድቦና መሬት አዘጋጅቶ ለምገባ ሊውል የሚችል ስራ ማስጀመሩን አድንቀዋል።

የአፋር ክልል ትምህርት ቢሮ ሃላፊ ሙሳ አደም በበኩላቸው፤ የምገባ መርሃ ግብሩን ለመደገፍ በዱብቲ የለማው ሰብል የምግብ ሉዓላዊነትን ከማረጋገጥ አኳያም ወሳኝነት ያለው ነው ብለዋል።

ሰፊ መሬትና በቂ ውሃ ሃብት እያለን ለምን አናለማም በሚል ተነሳሽነት በክልሉ አዋሽ ወንዝን ተከትለው የሚገኙ ትምህርት ቤቶች እያንዳንዳቸው 3 ሄክታር ተሰጥቷቸው ማልማት ጀምረዋል ሲሉ አስታውቀዋል።

ይኸንን ማጠናከር ላይ ትኩረት አድርገን እየሰራን ነው ሲሉም ገልጸዋል።

ሚኒስትር ዴኤታዋ ከጎብኝቱ ጎን ለጎን አስቦዳ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ተገኝተው የተማሪዎችን የምገባ መርሃ ግብር ተመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም