ኢትዮጵያ ኬንያን በማሸነፍ የምድቡ መሪ ሆና አጠናቀቀች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ኬንያን በማሸነፍ የምድቡ መሪ ሆና አጠናቀቀች
አዲስ አበባ፤ ሕዳር 17/2018(ኢዜአ)፦ በ16ኛው ከ17 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ የሴካፋ ማጣሪያ የምድብ አንድ ጨዋታ አዘጋጇ ኢትዮጵያ ኬንያን 1 ለ 0 አሸንፋለች።
በአበበ ቢቂላ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ዳዊት ካሳው በ64ኛው ደቂቃ ላይ የማሸነፊያዋን ጎል አስቆጥሯል።
ድሉን ተከትሎ አስቀድማ ወደ ግማሽ ፍጻሜ ያለፈችው ኢትዮጵያ በ10 ነጥብ ምድብ አንድን በመሪነት አጠናቃለች።
ኬንያ በሰባት ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች። ቡድኑ ለግማሽ ፍጻሜ ማለፉ ይታወቃል።
ኢትዮጵያ በግማሽ ፍጻሜው በምድብ ሁለት ሁለተኛ ደረጃን ይዛ ካጠናቀቀችው ዩጋንዳ ጋር እሁድ ሕዳር 21 ቀን 2018 ዓ.ም ትጫወታለች።
ታንዛንያ እና ኬንያ ሌላኛው የግማሽ ፍጻሜ መርሃ ግብር ነው።
የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሄራዊ ቡድን አጥቂ ዳዊት ካሳው በውድድሩ ላይ ያስቆጠራቸውን ግቦች ብዛት ወደ ሰባት ከፍ በማድረግ የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነቱን መምራት ጀምሯል።
በተያያዘም በምድብ አንድ ዛሬ በተደረገ ጨዋታ ደቡብ ሱዳን ሩዋንዳን 2 ለ 1 አሸንፋለች።