ኢትዮጵያ በዘላቂ የእንስሳት ሃብት ልማት በአርዓያነት የሚወሰድ ውጤት እያስመዘገበች ነው -የዓለም የእንስሳት ጤና ድርጅት - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በዘላቂ የእንስሳት ሃብት ልማት በአርዓያነት የሚወሰድ ውጤት እያስመዘገበች ነው -የዓለም የእንስሳት ጤና ድርጅት
አዲስ አበባ፤ ህዳር 17/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ዘላቂ የእንስሳት ሃብት ልማት በመገንባት ረገድ በአርዓያነት የሚወሰድ ውጤት እያስመዘገበች እንደምትገኝ የዓለም እንስሳት ጤና ድርጅት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ባባ ሱማሬ ገለጹ።
የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ህዝቦች ኑሮና ኢኮኖሚ በአብዛኛው ከእንስሳት ሃብት ልማት ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ነው።
የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ ደግሞ በምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የእንስሳት ሃብት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ በማሳደር ላይ እንደሚገኝ ይታወቃል።
ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ በአርብቶ አደር አካባቢዎች እንስሳት ሃብት ላይ የሚደርሰውን ተፅዕኖ ለመቀነስ በአረንጓዴ የኢኮኖሚ ስትራቴጂ የተደገፈ የመቋቋም አቅም እየገነባች ትገኛለች።
ለአብነትም በእንስሳት መኖና ውሃ ልማት፣ በዝርያ ማሻሻያና ጤና ጥበቃ፣ በማቆያና ገበያ ማዕከላት ግንባታ እንዲሁም በቅድመ ማስጠንቀቂያ የአየር ንብረት ተፅዕኖን የመቋቋም ሥርዓት እየዘረጋች ነው።
የዓለም እንስሳት ጤና ድርጅት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ባባ ሱማሬ ለኢዜአ እንደገለጹት÷ ኢትዮጵያ በዘላቂ የእንስሳት ሃብት ልማት አበረታች ውጤት እያስመዘገበች ነው።
በእንስሳት ሃብት ጥበቃና ምርታማነት ላይ የተተገበሩ የአሰራር ሥርዓቶች የዘርፉን ውጤታማነት በማሻሻል የሚታይ ለውጥ ማስገኘታቸውን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በድንበር ተሻጋሪ የእንስሳት እንቅስቃሴና ልማት ላይ በትብብር ለመስራት ያላት ቁርጠኝነት የሚደነቅ መሆኑን ጠቅሰው በተለይም በግጦሽ መሬትና በውሃ ሃብቶች ላይ የጋራ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ መስራት ይገባል ብለዋል።
በቀጣይም በእንስሳትና በሰው ጤና እንዲሁም በአካባቢ ጥበቃ ላይ የዓለም ጤና ድርጅት መርህን በመከተል ትብብርን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።
ኢትዮጵያ በእንስሳት ሃብት ልማት ላይ የወሰደችው የፖሊሲ ማሻሻያ ለሌሎች ሀገራት አርአያ የሚሆን ነው ብለዋል፡፡
ማሻሻያዎቹ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን በመቀነስ የአርብቶ አደሩን ተጠቃሚነት እያሳደጉ መምጣታቸውን ተናግረዋል።
የዓለም የእንስሳት ጤና ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ በእንስሳት ሃብት ላይ የሚያሳድረውን ጫና ለመቀነስ ድጋፍና ክትትል እያደረገ እንደሚገኝ አስረድተዋል።