ቀጥታ፡

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል እየተከናዎኑ የሚገኙ የልማት ሥራዎች የክልሉን የመልማት አቅም የሚያሳዩ ናቸው

አሶሳ፤ ህዳር 17/2018(ኢዜአ)፦በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ሥራዎች የክልሉን የመልማት አቅም የሚያሳዩ መሆናቸውን የክልሉ አመራሮች ተናገሩ።

"በመደመር መንግሥት እይታ የዘርፎች እመርታ" በሚል መሪ ሃሳብ ስልጠና ላይ የሚገኙ የክልሉ ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች በክልሉ እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ስራዎችን ጎብኝተዋል።

አመራሮቹ የኸልዋ የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ፣ ፍቃዱ ነመራ የተቀናጀ የእርሻ ልማት፣ ፄፄ የዶሮ ብዜት ማዕከል እና ሌሎች የልማት ስራዎችን ተመልክተዋል።

በጉብኝቱ ወቅት ያነጋገርናቸው አመራሮች በክልሉ እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ስራዎች የክልሉን የመልማት አቅም ወደ ውጤት የቀየሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ከአመራሮቹ መካከል አቶ ገዛኸኝ መኮንን እና ግዛቸው ላሉቶ ስልጠናው የገጠር ትራንስፎርሜሽን እሳቤን ወደ ላቀ ደረጃ በማሸጋገር የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የሚያግዝ መሆኑን ገልጸው በጉብኝታቸውም በክልሉ የተከናወኑ የልማት ስራዎች ይህንን በተግባር ያረጋገጡ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በተለይም በመደመር መንግስት እይታ የሚከናወኑ የልማት ስራዎች ሁሉንም ዘርፎች አካተቱ እና ውጤታማ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የአርሶ አደሩን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል እየተከናወነ የሚገኘው የተቀናጀ ግብርና ስራንም በሁሉም አካባቢ ማስፋት እንደሚጠበቅ ጠቁመዋል።

ሌላዋ የጉብኝቱ ተሳታፊ ሀጂራ ኢብራሂም እንደገለፁት፤ ስልጠናው አመራሩ ከክልሉ በተጨማሪ ሀገራዊ ገዳዮች ላይ የጠራ ግንዛቤ እንዲኖረው የሚያደርግ ነው ብለዋል።

በስልጠና ላይ ያገኙትን ልምድ ወደ ተግባር በመቀየር የክልሉ ሀብት ልማት ላይ ይብልጥ የሚውልበትን አቅም በመፍጠር ብልጽግናን ለማረጋገጥ እንደሚሰሩ አንስተዋል።

የክልሉ መንግስት እያከናወናቸው የሚገኙ የልማት ስራዎች የዜጎችን ኢኮኖሚ የሚያሳድጉ እንዲሁም ለስራ ዕድል ፈጠራ ጉልህ ሚና እየተጫወቱ ነው ያሉት ደግሞ ሌላው የጉብኝቱ ተሳታፊ አሳዬ አበበ ናቸው።

ጉብኝቱ የአመራሩን የሥራ ተነሳሽነት የሚጨምር እና በየአካባቢው የሚገኘውን ሀብት ወደ ልማት ለመቀየር ተሞክሮ የወሰዱበት እንደነበርም ገልጸዋል።

አመራሮቹ በመደመር ትውልድ መጽሐፍ ሽያጭ የተገነባውን የአሶሳ ህዳሴ ሙዜየም፣ የክልሉን ገጠር ቴክኖሎጂ ብዜትና የግብርና ሜካናይዜሽን ማስፋፊያ ኤጀንሲ እና የአሶሳ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የሥራ እንቅስቃሴንም ጎብኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም