ቀጥታ፡

በክልሉ የሕዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያግዙ ውጤታማ የልማት ተግባራት በመከናወን ላይ ይገኛሉ

ወላይታ ሶዶ ፤ ሕዳር 17/2018 (ኢዜአ):- በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሕዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያግዙ ውጤታማ የልማት ተግባራት በመከናወን ላይ እንደሚገኙ ተገለጸ።

"በመደመር መንግሥት እይታ የዘርፎች እመርታ" በሚል መሪ ሀሳብ በወላይታ ሶዶ ከተማ ስልጠና ሲከታተሉ የቆዩ ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች የልማት ስራዎችን እንቅስቃሴ ዛሬ ተመልክተዋል።

አመራሮቹ የተመለከቱት በክልሉ ወላይታ ሶዶ እና ቦዲቲ ከተማ የኢንዱስትሪ፣ የግብርና እና ሌሎች የልማት ስራዎችን ነው።

በምልከታው ላይ ከተሳተፉት አመራሮች መካከል ኢያሱ አበበ፤ ከለውጡ ወዲህ የዜጎችን ህይወት በመሰረታዊነት ለመለወጥ እየተከናወኑ ካሉ ተግባራት የግብርና ልማትን ለአብነት ጠቅሰዋል።

ይህም ከድህነት ለመውጣት የሚደረገውን ጥረት በጉልህ የሚደግፉና ተስፋ ሰጪ ነው ብለዋል።

በከተማው በኩታ ገጠም እየለማ ከሚገኘው የስንዴ ልማት በተጨባጭ አርሶ አደሮች እየተጠቀሙ ስለመሆኑ በማሳያነት አንስተዋል።


በከተማው በግብርና፣ በኢንዱስትሪና በሌሎችም ዘርፎች እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ውጤታማ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ አጸደ አይዛ ናቸው።

በክልሉ በስፋት የሚመረቱ የተለያዩ የግብርና ምርቶችን ለኢንዱስትሪ ግብዓትነት በማቅረብና በማስተሳሰር የታየው እመርታዊ ለውጥ አበረታች መሆኑን አንስተዋል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የመንግስት ረዳት ተጠሪ አቶ ንጋቱ ዳንሳ፤ በክልሉ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እየተከናወነ ያለው ስራ ውጤት እየታየበት መሆኑን ገልጸዋል።

በመኸሩ ወቅት ከ800 ሺህ ሄክታር በላይ ማሳ በስንዴ መልማቱን ጠቅሰው፤ በኢንዱስትሪና በቱሪዝም ዘርፎች ጭምር የመጡ ለውጦችን ለማስቀጠል አመራሩ በቁርጠኝነት የመምራትና የመፈፀም አቅሙን ማሳደግ እንዳለበት አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም