ቀጥታ፡

በኦሮሚያ ክልል የግብርናውን ዘርፍ በማዘመን ምርታማነትን ለማሳደግ የተጀመሩ ስራዎች ውጤታማ ሆነዋል

ጅማ፤ህዳር 17/2018(ኢዜአ)፦በኦሮሚያ ክልል የግብርናውን ዘርፍ በማዘመን ምርታማነትን ለማሳደግ የተጀመሩ ስራዎች ውጤታማ መሆናቸውን የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አወሉ አብዲ ገለጹ።

በጅማ ከተማ የስራ አስፈፃሚ ክህሎት ስልጠና መርሀ ግብር ላይ የተሳተፉ ከክልል ጀምሮ በየደረጃው ያሉ አመራሮች በጅማ ዞን የግብርና የልማት ስራዎችን እየጎበኙ ነው።

አመራሮቹ በሸቤ ወረዳ ኪሼ ቀበሌ እየተሰበሰበ ያለውን የሩዝ ልማት ጎብኝተዋል።

በጉብኝቱ ላይ የተገኙት የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አወሉ አብዲ እንዳሉት፥ የግብርናውን ዘርፍ በማዘመን ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሰራ ነው።

በክልሉ የተጀመሩት የግብርና ኢኒሼቲቭ ስራዎች ምርታማነትን በማሳደግ ረገድ ውጤት እየተመዘገበባቸው መሆኑን ተናግረዋል።

የበጋ ስንዴና የክረምት ሩዝ ልማት በክልሉ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ መሆኑን አንስተው፥ ይህም ምርታማነትን በማሳደግ በምግብ ራስን ለማቻል ትልቅ ሚና አለው ብለዋል።

በግብርናው ዘርፍ እየተተገበሩ ያሉ ኢኒሼቲቮችን በማሳካት ዘርፉን የበለጠ ውጤታማ ለማድረግ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የተጀመሩት የግብርና ኢኒሼቲሾች የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ እና ሰፊ የስራ እድል በመፍጠር ተጨማሪ አቅም መፍጠር ችለዋል ብለዋል።

በጉብኝቱ ከክልል ጀምሮ በየደረጃው ያሉ አመራሮች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም