ኢትዮጵያና ፈረንሳይ በሁሉም መስኮች ያላቸው ትብብር እያደገ መጥቷል - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያና ፈረንሳይ በሁሉም መስኮች ያላቸው ትብብር እያደገ መጥቷል
አዲስ አበባ፤ ህዳር 17/2018(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያና ፈረንሳይ በባህል፣ትምህርትና ኢኮኖሚን ጨምሮ በሌሎች መስኮች ያላቸው ትብብር እያደገ መምጣቱን በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ ገለጹ።
አቶ አደም ፋራህ በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር ከሆኑት አሌክሲስ ላሜክ ጋር ተወያይተዋል።
በብልጽግና ፓርቲ ዋና ጽህፈት ቤት በተካሄደው ውይይት የሁለቱ ሀገራት ግንኙነትን ይበልጥ በሚያጠናክሩ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት ተደርጓል።
ፈረንሳይ እና ኢትዮጵያ በንግድና ኢንቨስተመንት፣በባህልና ቅርስ ጥበቃ ዘርፍ፣በሲቪል አቪዬሽን እንዲሁም በፖለቲካ ዲፕሎማሲ መስኮች ጠንካራ ትብብር ያላቸው ሀገራት መሆኑን አቶ አደም በዚሁ ጊዜ አንስተዋል።
የላሊበላ ውቅር አብያተ ቤተክርስቲያናት ዕድሳት ስኬታማ እንዲሆን ፈረንሳይ ላደረገችው ድጋፍም ምስጋና አቅርበዋል።
በትምህርት እና ሳይንስ መስክም ሀገራቱ ጥብቅ ትስስር ያላቸው መሆኑን የጠቀሱት አቶ አደም፤የሊሴ ገብረማርያም ትምህርት ቤት፣ አሊያንስ ኢትዮ ፍራንሲስ የባህል ማዕከል እንዲሁም የጥናት ማዕከል በኢትዮጵያ መቋቋሙን ለአብነት ጠቅሰዋል።
በሀገር አቀፍ ደረጃ ተግባራዊ በተደረገው የሪፎርም ሥራዎች በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚና ፖለቲካ መስኮች ተጨባጭ ውጤቶች እየመጡ መሆኑንም አብራርተዋል።
የኢኮኖሚ ሪፎርሙ ውጤታማ እንዲሆን የፈረንሳይ ድጋፍ ትልቅ መሆኑን አስታውሰው፤ትብብሩ በሌሎችም መስኮች ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
በተለይም በዘላቂ ልማት፣ሰው ሰራሽ አስተውሎት(ኤ አይ)ን ጨምሮ በተለያዩ ቴክኖሎጂዎች ላይ ሀገራቱ በላቀ ደረጃ ተሳስረው ሊሰሩ እንደሚገባ ያነሱት አቶ አደም ለዚህም ቁርጠኛ ነን ብለዋል።
የብልፅግና ፓርቲም የሁለቱ ሀገራት ትብብር ወደ ላቀ ደረጃ እንዲሸጋገር የበኩሉን ሚና እንደሚወጣም አረጋግጠዋል።
በፖለቲካ መስክም ምህዳሩን ለማስፋት የለውጡ መንግሥት ተጨባጭ እርምጃዎች መውሰዱን ጠቁመው፤ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አባላት የካቢኔ አባል ሆነው እንዲሰሩ መመቻቸቱን ለአብነት ጠቅሰዋል።
የዲሞክራሲ ተቋማት ማጠናከር ላይም ስኬታማ ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸው፤ የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ እንዲሁም የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን እንዲጠናከሩ አስፈላጊው ድጋፍ እየተደረገ ነው ብለዋል።
በቀጣይ የሚካሄደው 7ኛው ሀገራዊ ምርጫ ዲሞክራሲያዊ፣ ፍትሃዊና ተአማኒ እንዲሆን ብልፅግና ፓርቲ በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑንም አብራርተዋል።
በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር አሌክሲስ ላሜክ በበኩላቸው፤የኢትዮጵያና ፈረንሳይ በተለይም ባለፉት ሰባት ዓመታት በተለያዩ መስኮች ያላቸው ግንኙነት እየተጠናከረ መምጣቱን ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በፈረንሳይ ያደረጉት ጉብኝት እንዲሁም የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በኢትዮጵያ ያደረጉትን ጉብኝትን ተከትሎ የሀገራቱ ግንኙነት ይበልጥ መጠናከሩን አስረድተዋል።
በቅርቡ በደቡብ አፍሪካ በተካሄደው የቡድን 20 አባል ሀገራት ጉባኤ ላይ የሀገራቱ መሪዎች ግንኙነቱን የሚያሳድጉ ፍሬያማ ውይይት ማድረጋቸውንም አስታውሰዋል።
በኢትዮጵያ በሁሉም መስክ እየመጡ ያሉ ለውጦች የሚበረታቱ መሆኑን የጠቆሙት አምባሳደር አሌክሲስ፤ ይህ ትስስር ተጠናክሮ እንዲቀጥል በቁርጠኝነት እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።
በኢትዮጵያ በዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ፣ ተቋማትን ማጠናከር፣ ባህል ልውውጥ እንዲሁም በፓርቲ ዲፕሎማሲ ዙሪያ ፈረንሳይ ከኢትዮጵያ ጋር አብራ ለመሥራት ዝግጁ መሆኗንም አመልክተዋል።