ቀጥታ፡

በምስራቅ ሐረርጌ ዞን በዘንድሮው የበጋ መስኖ 96 ሺህ ሄክታር መሬት በስንዴ ይለማል

ጉርሱም፤ህዳር 17/2018 (ኢዜአ)፦በምስራቅ ሐረርጌ ዞን በዘንድሮ የበጋ መስኖ 96 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ስንዴ እንደሚለማ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አስታወቀ።

በዞኑ የበጋ ወራት የመስኖ ስንዴ ልማት አካል የሆነውና በሜካናይዜሽን የታገዘ በዘር የመሸፈን ስራ ዛሬ በጉርሱም ወረዳ ሀሮ ባቴ ቀበሌ ተጀምሯል።

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ወይዘሮ ሚስኪ መሐመድ በዚህ ወቅት እንደገለጹት፤ በዞኑ የሚከናወነው የስንዴ ልማት ስራ በየዓመቱ እያደገ ይገኛል።

የስንዴ ልማቱ የአርሶ አደሩን የምግብ ዋስትና ከማረጋገጥ ባለፈ በስራው ለተሳተፉ ወጣቶች ገቢ በማስገኘት የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸውን እያሳደገ መሆኑን ተናግረዋል።

በዞኑ በግብርና ዘርፍ ያለውን የሰው ሃይል፣ የውሃ አማራጮችንና ያልታረሱና ፆም ያደሩ መሬቶችን በተገቢው መንገድ በመጠቀም የተሻለ ምርት ለማግኘት እንደሚሰራም ገልጸዋል።

የበጋ መስኖ የስንዴ ልማቱን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ ትኩረት መሰጠቱን የተናገሩት ዋና አስተዳዳሪዋ ለዚህም አመራሩ ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል ብለዋል።

በበጋ ወራቱ በዞኑ በሁሉም ወረዳዎች በ96 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ስንዴ በኩታገጠም እንደሚለማ ገልጸው፤ በዚህም በሚካናይዜሽን በመታገዝ ወደ ስራ መገባቱን አስታውቀዋል።

አርሶ አደሩም የጉድጓድ ውሃና ጥቃቅን የመስኖ ግድቦችን በመጠቀም እቅዱን ስኬታማ ለማድረግ በቁርጠኝነት ይሰራል ብለዋል።

ለስንዴ ልማቱም አሰፈላጊው የምርት ግብዓት መቅረቡን ጠቁመው ለስንዴ ልማቱም የግብርና ባለሙያው፣ አርሶ አደሩና አመራሩ ተቀናጅቶ ተግባራዊ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

በመርሃ ግብሩ የክልል፣የዞንና የወረዳ አመራር አካላት፣ የግብርና ባለሙያዎች፣ አርሶአደሮችና ሌሎች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም