ቀጥታ፡

በህብረ ብሄራዊነት ጠንካራ ሀገረ መንግስት በመገንባት ሂደት ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል

አዳማ ፤ ሕዳር 17/2018(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ አሰባሳቢና ገዥ ትርክትን በስፋት በማስረጽ በህብረ ብሄራዊነት ጠንካራ ሀገረ መንግስት  በመገንባት ሂደት ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ ተገለጸ።

የፌዴራልና የክልል የሲቪል ሰርቪስ ተቋማት የስራ ሃላፊዎችና ባለሙያዎች የተሳተፉበት "የጋራ ትርክት ለጋራ  ሀገር" በሚል መሪ ሃሳብ የውይይት መድረክ በአዳማ እየተካሄደ ነው።


 

በመድረኩ ላይ በመገኘት ንግግር ያደረጉት በሰላም ሚኒስቴር የሰላም ግንባታና ብሄራዊ መግባባት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አማካሪ አቶ ፍሬሰንበት ወልደተንሳይ፤  በለውጡ ዓመታት በጠንካራ ህብረ ብሄራዊ አንድነት የሀገርን ልማትና ብልጽግና ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ዘርፈ ብዙ ተግባራት መከናወናቸውን አንስተዋል።


 

በተቋማት ግንባታ ረገድም በሲቪል ሰርቪስና የዴሞክራሲ ተቋማት ሪፎርም በማድረግ ጠንካራ መሰረት ይዘው እንዲዘልቁ ለማስቻል የተቀናጀ ጥረት መደረጉን ገልጸዋል።

በመሆኑም በቀጣይም ሰላምን የማጽናት፣ የተቋማት ግንባታ የማጠናከርና የሀገረ መንግስት ግንባታ ስራዎች ተጠናክረው የሚቀጥሉ መሆኑን ተናግረዋል። 

በኢትዮጵያ አሰባሳቢና ገዥ ትርክትን በስፋት በማስረጽ በህብረ ብሄራዊነት ጠንካራ ሀገረ መንግስት መገንባት ይገባል ሲሉ አስገንዝበዋል።

በመድረኩ ላይ የተገኙት የኦሮሚያ ክልል አስተዳደርና ፀጥታ ቢሮ ተወካይ ባልቻ ቀነኒ (ዶ/ር) ፤  ሰላምን በማጽናትና ዘርፈ ብዙ የልማት ስራዎችን በማከናወን እመርታዊ ለውጥ እውን እየሆነ ነው ብለዋል።


 

በክልሉ ልማትን ከማጽናት ባሻገር በሰው ሃይል ግንባታና የቴክኖሎጂ ልማት ላይ በማተኮር በመሰራቱም ለውጥ መምጣቱን ገልጸዋል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ የሰላም ግንባታ ዳይሬክተር አቶ ጌታነህ መንቴ በበኩላቸው፤በለውጡ ዓመታት ሰላምን በዘላቂነት በማጽናት የተቋማት ግንባታና የአገልግሎት አሰጣጥ ላይ በትኩረት ተሰርቶ ውጤትም መምጣቱን አንስተዋል።


 

በቀጣይም ከዋልታ ረገጥ እሳቤና ከመነጣጠል በመውጣት ህብረ ብሄራዊ አንድነትን በማጽናት ለጋራ ልማት መትጋት ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም