ቀጥታ፡

በክልሉ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎች መነቃቃትን ፈጥረዋል 

ሰመራ፤ ሕዳር 17/2018(ኢዜአ)፦ በአፋር ክልል እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎች የህዝብ ተጠቃሚነትን ያረጋገጡና ለቀጣይ ልማት መነቃቃት የፈጠሩ መሆናቸውን ተመልክተናል ሲሉ የስልጠና ተሳታፊ አመራሮች ተናገሩ።

"በመደመር መንግስት እይታ የዘርፎች እመርታ" በሚል መሪ ሐሳብ በአፋር ክልል የሁለተኛ ዙር የከፍተኛና መካከለኛ አመራር ስልጠና እየወሰዱ ያሉ የአመራር አካላት በክልሉ የተሰሩ የልማት ስራዎችን እየተመለከቱ ነው።


 

ከጉብኝቱ ተሳታፊዎች መካከል ከገቢ ረሱ ዞን የመጡት ወይዘሮ ሃዲ ሀሰን ለውጡን ተከትሎ በአፋር ክልል ፀጋዎችን መጠቀም ተጀምሯል ብለዋል።


 

በተለይም በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር እየተከናወነ ያለው ስራ የአርብቶ አደሩን ህይወት በትክክል መለወጥ እንደሚቻል ማሳያ ነው ብለዋል።

በማሳያነትም በዘርፉ የተሰማሩት ዜጎች የወተት፣ የስጋና የእንቁላል ምርቶችን በአቅራቢያቸው ላሉ ከተሞች በማቅረብ ተጠቃሚነታቸውን እያሳደጉ መምጣታቸውን ተመልክተናል ብለዋል።

ከሚሌ ከተማ አስተዳደር የመጡት አቶ ሃፋ መሐመድ በበኩላቸው በክልሉ በግብርናና ኢንዱስትሪ ዘርፍ የተከናወኑ ተግባራት አበረታች መሆናቸውን ገልጸዋል።


 

የልማት ተግባራቱ በክልሉ ያሉ ዕምቅ ሃብቶችን በመጠቀም ተጠቃሚነትን ማሳደግ የሚያስችሉና ለቀጣይ ልማት መነቃቃት የፈጠሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ከኸሪ ራሱ ዞን የመጡት ሃሚድ መሐመድ በበኩላቸው፤ በክልሉ ከተሞች እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማትና የተገነቡ ፋብሪካዎች የለውጡ መንግስት ትሩፋቶች ውጤታማነት ማሳያ ናቸው ብለዋል።


 

የክልሉን ዕምቅ አቅም ባገናዘበ መልኩ የተከናወኑ ልማቶች መሆናቸውን ገልጸው፤ ይህም የህዝቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ናቸው ብለዋል።

እነዚህን ስራዎች አመራሩ በየደረጃው ወደ ወረዳ እና ቀበሌዎች በማውረድ መስራት እንዲችል ከምልከታው  የተወሰደው ልምድና ተሞክሮ የሚያነቃቃ ነው ብለዋል።

በጎብኝቱ መርሃ ግብር ላይ በብልፅግና ፓርቲ የአፋር ክልል ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ሃላፊ አቶ መሐመድ ሁሴንን ጨምሮ፣ ሌሎች ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም