ቀጥታ፡

የባሕር ዳር ከተማን ዘላቂ እድገት የሚያረጋግጡ የተለያዩ የልማት ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ

ባሕርዳር፤ ሕዳር 17/2018(ኢዜአ) ፡- የባሕር ዳር ከተማን ዘላቂ እድገት በሚያረጋግጥ አግባብ  የተለያዩ የልማት ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ  የከተማ አስተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ  ጎሹ እንዳላማው ገለጹ። 

በ“ የመደመር መንግስት እይታ የዘርፎች እመርታ” በሚል መሪ ሀሳብ ስልጠና ሲከታተሉ የቆዩ የአማራ ክልል ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች በባሕር ዳር ከተማ የተከናወኑ የልማት ስራዎችን ተዘዋውረው ተመልክተዋል።

አመራሮቹ  ከተመለከቷቸው  መካከልም የባሕር ዳር ኮሪደር ልማት፣ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት፣ የራባል ብረታ ብረት፣ ኮከብ ኢንዱስትሪ ግራናይት ማምረቻ ፋብሪካ እና ሌሎችም ይጠቀሳሉ።


 

ከጉብኝቱ በኋላ ማብራሪያ የሰጡት የባሕር ዳር ከተማ  ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው፤ የልማት ሰራዎቹ ከተማዋን ለነዋሪዎች፣ ለጎብኝዎች እና ለኢንዱስትሪ ልማት ምቹ የማድረግ ጥረት መሆናቸውን ገልጸዋል።

በከተማው በዚህ ዓመት የ42 ትላልቅ ፕሮጀክቶች ስራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰው፤  ለፕሮጀክቶቹ ከመንግስት በተጨማሪ ነዋሪዎች፣  ባለሀብቶችና ተቋማት  ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።


 

በከተማው በልዩ ክትትልና ቁጥጥር እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት የመንግስት ፕሮጀክቶችን ጀምሮ ማጠናቀቅ ርዕይ በተግባር የተረጋገጠበት መሆኑንም አንስተዋል።

የባሕር ዳር ከተማን ዘላቂ እድገት በሚያረጋግጥ አግባብ  የተለያዩ የልማት ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ገልጸዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም