የማርበርግ ቫይረስን በአጭር ጊዜ ውስጥ መከላከልና መቆጣጠር የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የማርበርግ ቫይረስን በአጭር ጊዜ ውስጥ መከላከልና መቆጣጠር የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው
አዲስ አበባ፤ ሕዳር 17/2018(ኢዜአ)፦ የማርበርግ ቫይረስን በአጭር ጊዜ ውስጥ መከላከልና መቆጣጠር የሚያስችሉ ተግባራት በስፋት እየተከናወኑ መሆኑን የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ገለፁ።
የማርበርግ ቫይረስን ወቅታዊ ሁኔታና እየተሰሩ ያሉ የመከላከል ስራዎችን በተመለከተ የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር መቅደስ ዳባ እና የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሳይ ኃይሉ መግለጫ ሰጥተዋል።
በዚህ ወቅት የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር መቅደስ ዳባ እንዳሉት የማርበርግ ቫይረስ በሽታ መከሰቱ ከተገለፀበት ጊዜ አንስቶ የክትትል ስራዎች ተጠናክረው ቀጥለዋል።
ቫይረሱን በአጭር ጊዜ መቆጣጠር የሚያስችሉ የልየታ፣ የህብረተሰብ ጤና አጠባበቅ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በባለሙያዎች የተደራጀ የምላሽ ሰጪ ቡድን የህብረተሰቡን ግንዛቤ ማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውንም ገልፀዋል።
እስከዛሬ ጠዋት ባለው ሰባ ሶስት ሰዎች ምርመራ ተደርጎ አስራ አንድ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው መረጋገጡንና የስድስት ሰዎች ህይወት ማለፉን አስረድተዋል።
ከታማሚዎች ጋር ንክኪ የነበራቸው ሶስት መቶ አርባ ዘጠኝ ሰዎች ተለይተው ክትትል እየተደረገላቸው መሆኑን ገልፀው አንድ መቶ አስራ ዘጠኝ ሰዎች የክትትል ጊዜ ገደብ ጨርሰው ከልየታ ማቆያ መውጣታቸውን ተናግረዋል።
በተንቀሳቃሽ ላቦራቶሪ ምርመራ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመው፤ የላቦራቶሪ ምርመራዎችን ለማጠናከር በስፋት እንደሚሰራም ነው የገለፁት።
በሽታው ተከስቶባቸው ከነበሩ ሀገራት ጋር ልምድ ልውውጥ በማድረግ ተጋላጭነትን የሚቀንሱና ለህክምና የሚሆኑ አስፈላጊ መድኃኒቶችን ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት ተደራሽ መደረጉንም አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሳይ ኃይሉ በበኩላቸው፤ የማርበርግ ቫይረስን የመከላከል፣ ቅኝት፣ ምላሽና ህብረተሰቡን የማስገንዘብ ስራዎች ተጠናክረው መቀጠላቸውን ተናግረዋል።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የቤት ለቤት ቅኝት እየተካሄደ መሆኑንና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።