ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በቡድን 20 ጉባኤ መሳተፏ ዓለም አቀፍ ተደማጭነቷ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ለመድረሱ ማሳያ ነው

አዲስ አበባ፤ ህዳር 17/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በቅርቡ በደቡብ አፍሪካ በተካሄደው የቡድን 20 ጉባኤ ላይ መሳተፏ የሀገሪቱ የዲፕሎማሲ አቅምና ዓለም አቀፍ ተደማጭነት ከፍተኛ ደረጃ ላይ ለመድረሱ ማሳያ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ጃፋር በድሩ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) እና የልዑክ ቡድናቸው በደቡብ አፍሪካ በተካሄደው የቡድን 20 ጉባኤ የተሳተፉ ሲሆን ከጉባኤው በተጓዳኝ ከበርካታ ሀገራትና ዓለም አቀፍ ተቋማት መሪዎች ጋርም ስኬታማ ውይይት ማድረጋቸው ይታወቃል።

የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ጃፋር በድሩ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ ቡድን 20 ከ80 በመቶ በላይ የዓለማችንን ኢኮኖሚ የሚያንቀሳቅሱ ሀገራትን ያሰባሰበ መድረክ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የዓለምን የኢኮኖሚና የፋይናንስ አቅጣጫ የሚወስኑ፣ በተለይም የልማት ፋይናንስና የኢኮኖሚ ጉዳዮች የሚበየኑበት ወሳኝ ቡድን ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ በመድረኩ ያደረገችው ፍሬያማ ተሳትፎ በዓለም አቀፍ መድረኮች ያላት ተደማጭነትና ተጽዕኖ እያደገ መምጣቱን ማሳያ መሆኑንም ተናግረዋል።

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ከጉባኤው በተጓዳኝ ከሀገራትና ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር የነበራቸው የሁለትዮሽ ውይይት የልማት ፋይናንስ ትብብርንና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን ይበልጥ የሚያጠናክር ውጤት የተገኘበት መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በጉባኤው ባስተላለፉት መልዕክት ኢትዮጵያና አፍሪካ በከፍታ ጎዳና ላይ መሆናቸውን በአፅንኦት እንዳነሱ ጠቅሰዋል።

በተለይም በከተማ ልማት፣ በግብርና፣ በአምራች ኢንዱስትሪ እና በዲጂታል ስርዓተ ምህዳር ተስፋ ሰጪ ለውጦች መኖራቸውን ለቡድን 20 አባል ሀገራት አስገንዝበዋል ነው ያሉት።

በዚህም ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረኮች ከራሷ አልፎ የአፍሪካን የልማት አጀንዳዎች በማሰማት በጎ ተፅዕኖ እየፈጠረች ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ በመድረኩ ይፋዊ መልዕክት እንድታስተላልፍ መጋበዟ የዲፕሎማሲ አቅሟ የደረሰበትን ከፍተኛ ደረጃና ተደማጭነት እንዲሁም ሀገራዊ ክብራችን እየጨመረ መምጣቱን የሚያመላክት መሆኑንም ተናግረዋል።

የቡድን 20 ጉባኤ ስኬታማ ተሳትፎዋም ሀገሪቱ ዲፕሎማሲዋ እያንሰራራ መሆኑን ያመለክታል መሆኑንም ገልጸዋል።

አቶ ጃፋር ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም በብሪክስ መድረክ ተጋብዛ አባል መሆኗን አስታውሰዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም