ቀጥታ፡

ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች ጥራት ያላቸው የውጭ ኢንቨስተሮች መዳረሻ ሆነዋል 

አዲስ አበባ፤ ሕዳር 17/2018(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች ጥራትና ብቃት ያላቸው የውጭ ኢንቨስተሮች መዳረሻ መሆናቸውን የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ታረቀኝ ቡሉልታ ገለጹ።

የኢትዮጵያ ሀገር በቀል የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ንግድና ኢንቨስትመንትን በማነቃቃት የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሃብቶች በልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች የሚሰማሩበትን ምቹ ምኅዳር ፈጥሯል።

በዚህም የኢትዮጵያ የዕድገት ምሰሶ ተደርገው ከተወሰዱ የግብርና፣ ማዕድን፣ ዲጂታል ቴክኖሎጂ፣ ቱሪዝም መስኮች ውስጥ የኢንዱስትሪ ምርታማነት ግንባር ቀደሙ መሆኑ ይታወቃል።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ታረቀኝ ቡሉልታ፤ ለልዩ ኢኮኖሚ ዞኖች ልማት የተሰጠው ትኩረት ዘርፉ ለሀገር ዕድገት ገንቢ ሚና እንዲወጣ እያስቻለ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የኢንዱስትሪ ምርታማነትና የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች የኢንቨስትመንት ዕድገትም በተኪ ምርት፣ በሥራ ዕድል ፈጠራና በወጪ ንግድ ተወዳዳሪነት ከፍተኛ ዕድገት እየተመዘገበ መሆኑን ተናግረዋል።

አሥራ ሦስት በመንግስት እንዲሁም ሰባት በግል ባለሃብቶች የሚተዳደሩ ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች የግብርና ምርት ማቀናባበርን ጨምሮ የዘርፉን ምርታማነት በማሳደግ አዎንታዊ ሚና እየተጫወቱ ነው ብለዋል።

ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች የኃይል መሠረተ ልማት አቅርቦትም በኢንቨስትመንት የተሰማሩ አልሚዎች የምርት ጥራትን ታሳቢ በማድረግ በሙሉ አቅማቸው የሚያመርቱበትን ዕድል እንደተፈጠረ አንስተዋል።

ለአብነትም በሀዋሳ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ኢንቨስትመንት የተሰማራው የጃፓኑ የሶላር አምራች ኩባንያ "ቶ ሶላር" ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ የታዳሽ ኃይል የገበያ አቅርቦት ወሳኝ ተዋናይ እያደረጋት ነው ብለዋል።

በቀጣይም በውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት አቅምና ጥራት ያላቸው አልሚዎችን በመሳብ ምቹ ድጋፍ የማድረግ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስረድተዋል።

የሀገር ውስጥ አልሚ ባለሃብቶችም በኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚኖራቸውን ተሳትፎ የሚያሳድግ አሰራር በመዘርጋት የዘርፉን ሽግግር ውጤታማነት ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ለሀገር ውስጥ ባለሃብቶች የተፈጠረው ምቹ የኢንቨስትመንት አሰራርም በኢንዱስትሪ ፓርኮች ያላቸውን ተሳትፎ በከፍተኛ መጠን እያሻሻለ መሆኑን አስረድተዋል።

በግብርና ምርት ማቀነባበር ዘርፍ የተሰማሩትን ጨምሮ በኢንዱስትሪ ዘርፍ የተፈጠረው መነቃቃት የተኪ ምርትና የወጪ ንግድ ተወዳዳሪነትን በማሳደግ ትልቅ ድርሻ መያዛቸውን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ በተኪ ምርት እየተፈጠረ የሚገኘው የኢንዱስትሪ ምርታማነት አቅም የሀገር ውስጥ ምርቶችን የመጠቀም ባህል እያሳደገ እንደሚገኝም ሚኒስትር ዴኤታው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም