የአፍሪካ ሕገ-መንግስታዊ ፍርድ ቤቶችና መሰል ተቋማት ዓለም አቀፍ ሲምፖዝየም በአዲስ አበባ ይካሄዳል - ኢዜአ አማርኛ
የአፍሪካ ሕገ-መንግስታዊ ፍርድ ቤቶችና መሰል ተቋማት ዓለም አቀፍ ሲምፖዝየም በአዲስ አበባ ይካሄዳል
አዲስ አበባ፤ ሕዳር 17/2018(ኢዜአ)፦የአፍሪካ ሕገ-መንግስታዊ ፍርድ ቤቶችና መሰል ተቋማት ዓለም አቀፍ ሲምፖዝየም በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ የኢፌድሪ ሕገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ አስታወቀ።
አጣሪ ጉባኤው 4ኛውን የአፍሪካ ሕገ-መንግስታዊ ፍርድ ቤቶችና መሰል ተቋማት ዓለም አቀፍ ሲምፖዝየም አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙኅን መግለጫ ሰጥቷል።
መግለጫውን የሰጡት የኢፌድሪ የህገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ደሳለኝ ወዬሳ፤ ሲምፖዝየሙ ህዳር 19 በአፍሪካ ሕብረት የመሰብሰቢያ አዳራሽ መካሄድ ይጀምራል ብለዋል።
በሲፖዝየሙ የአባል ሀገራቱ የሕገ-መንግስታዊ ፍርድ ቤቶች ፕሬዝደንቶች፣ በዓለም አቀፍ ተቋማት የሚሰሩ የዘርፉ ምሁራን እንዲሁም ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እንደሚታደሙ ተናግረዋል።
የአፍሪካ ሕገ-መንግስታዊ ፍርድ ቤቶችና መሰል ተቋማት ዓለም አቀፍ ሲምፖዝየም "ሕገ-መንግስታዊነትና ሀገረ መንግስት ግንባታ" በሚል መሪሃሳብ እንደሚካሄድ አስታውቀዋል።
በመድረኩ ኢትዮጵያም ከምታጋራው ተሞክሮ በተጨማሪ በዘርፉ ላይ የተደረጉ በርካታ የምርምር ውጤቶች ቀርበው ውይይት እንደሚደረግባቸው አመላክተዋል።
በሲምፖዝየሙ ለመሳተፍም እንግዶች ወደ ኢትዮጵያ እየገቡ እንደሚገኙ ጠቁመው፤ ተሳታፊዎች በሚኖራቸው ቆይታ በአዲስ አበባ የተለያዩ ስፍራዎችን እንደሚጎበኙ አስረድተዋል።
ሲምፖዝየሙን በተሳካ መንገድ ለማካሄድም አስፈላጊ ቅድመ ዝግጅቶች መጠናቀቃቸውን ተናግረዋል።